የታክስ ኦዲት ጥራትን ለማስጠበቅ አዲስ አሰራር መዘርጋቱ ተገለፀ

የገቢዎች ሚኒስቴር 400 ከሚሆኑ የታክስ ኦዲት ባለሙያዎች ጋር በሙያዊ ስነ-ምግባር፣ በግብረገብነትና በሃላፊነት ዙሪያ ምክክር አካሂዷል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የታክስ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበበ ለዋልታ እንደገለፁት፤ ምክክር መድረኩ በዋናነት በሶስቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እና በ2011 በጀት ዓመት የታዩ ጉድለቶችና ጥንካሬዎች ተለይተው በተለይም የተግዳሮቶቹ መንስኤዎችን ለመድፈን ያለመ ነው፡፡

በተለይም መድረኩ ሙያዊ ስነ-ምግባር፣ ግብረገብነት እና ህጋዊ ሃላፊነቶች ላይ የሚስተዋሉ አሉታዊ ተግባራትን በማስተካከል በታክስ ኦዲት ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለማረም የሚያሰስችል ነው ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ባለሙያዎች ላይ የስነ-ምግባር ክፍተት እንዳለ ጥቆማ እንደሚደርሳቸው የገለፁት ዳይሬክተሩ ፤ መድረኩ ሰራተኞች ለህሊና እና ለስነ-ምግባር ተገዢ በመሆን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

የታክስ ኦዲት ጥራትን ለማስጠበቅም አዲስ አሰራር ተዘርግቶ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ያደጉ ሀገራት ከባለሙያዎቹ ጋር  ተቀራርበው እንደሚሰሩ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ጠቅሰው በኢትዮጵያም ከተቋሙ ውጪ  ካሉ ተመሳሳይ የሂሳብ አዋቂዎች ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡