የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ለ152ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እዉቅና ሰጠ

በእውቅና ስነስረአቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ "ግብርን በመደበቅ ሰላማችሁን የምታጡ ነጋዴዎች ግብርን በመክፈል ሰላማችሁን ግዙ"ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን በ2011 ዓ.ም በታማኝነት በግንባር ቀደም ግብራቸዉን በአግባቡ ክፍሏል ያላቸዉን ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችና የግብር አምባሳደሮች ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል እዉቅናና ሽልማት ሰቷቸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተዉ ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮቹ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኦሮሚያ በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለበትና ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ያለበት ክልል እንደመሆኑ በክልሉ በሚመረተዉ ኢኮኖሚ ልክ ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም ብለዋል፡፡

ግብር ለአንድ አካል የሚከፈል ሳይሆን ለህዝብ የሚከፈል በመሆኑ መሰረተ ልማትን ለማሟላትና ለዜጎቻችሁ በግብራችሁ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ የምትገነቡ ስለሆናችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል፤ብለዋል፡፡
በታማኝነት ግብርና ታክስን በአግባቡ የምትከፍሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች ወደ የትኛዉም የክልሉ ቢሮዎች ለአገልግሎት ስትመጡ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸዉና የክልሉ መንግስት ለሚፈልጉት አገልግሎት ተገቢዉን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸዉ ገልጧል፡፡
የክልሉ የገቢዎች ባለስልጣን ሃላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸዉ አገራችን በአፍሪካ ካሉ አገራት ግብርን በመስብስበ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ ከአገሪቱ እድገት አንፃር ተገቢዉ ግብር እየተሰበሰበ ባለመሆኑ ለግብር ትኩረት ተሰቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር ምኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ አባ ገዳዎች ፤ታዋቂ አትሌቶችና አርቲስቶች ተገኝተዋል፡፡