ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያና ጂፒኤስ ሳይገጠምላቸው ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተዘጋጀው መመሪያ ተግባራዊ መሆን ጀመረ

ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ እና ጂፒኤስ ሳይገጠምላቸው ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ያዘጋጀውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

መመሪያው ታህሳስ ፣2011 ዓ.ም አጋማሽ የፀደቀ ቢሆንም ተግባራዊ መሆን የጀመረው  ከሀምሌ 2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ነው ተብሏል፡፡

መመሪያው ከመውጣቱ በፊት የግዥ ጥያቄ ያቀረቡና የግዥ ሂደት የጀመሩ የተሸከርካሪ አስመጪዎች  መመሪያው አይመለከታቸውም ተብሏል፡፡

አዲሱ ቴክኖሎጂ በትራፊክ አደጋ ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመከላከል እንደሚረዳ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ይሄይስ ገልጸዋል፡፡

በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል መንግስት ግንዛቤ ማስጨበጥን ጨምሮ መሳሪያውን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ነው አቶ ሙሴ የገለፁት፡፡

መንግስት ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር የፍጥነት መገደቢያ እና ጂፒኤስ ቴክኖሎጂው ተገጥሞ ወደ ሃገር ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለሃብቶች የፍጥነት መገደቢያና ጂፒኤስ መሳሪያውን በተሽከርካሪዎች ላይ አስገጥመው በማስገባት በተመጣጣኝ ክፍያ ደንበኞቻቸውን የሚያስከፍሉበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ መገባቱም አቶ ሙሴ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡