የውጪ ሃገራት ገንዘቦችን በህገ ወጥ መንገድ ሲመነዝሩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የውጪ ሃገራት ገንዘቦችን በህገ ወጥ መንገድ ሲመነዝሩ ከነበሩ ግለሰቦች ላይ  7 ሚሊየን 600 ሺህ የኢትዮጵያ ብር በላይ እና 53 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በኮሚሽኑ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የማረጋገጥና የመከታተል ስራ በመስራትና ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በተጠርጣሪዎቹ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ነው የተጠቀሰው ገንዘብ የተገኘው፡፡

7 ሚሊየን 608 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እና 53 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችን ከገንዘብ መቁጠሪያ ማሽን ጭምር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሃላፊ ኮማንደር አወል አህመድ አስታውቀዋል፡፡
 

ተጠርጣሪዎቹ የውጪ ሃገራት ዜጎች የሚበዙባቸውን አካባቢዎች በጥናት በመለየትና ቪላ ቤቶችን በመከራየት በህገ ወጥ መንገድ የውጪ ሃገራት ገንዘቦችን የመመንዘር ተግባር ሲያከናውኑ እንደነበርም ተብራርቷል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ደላሎችን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑንና  የምርመራው ውጤቱ የደረሰበትን ደረጃ በቀጣይ ለህብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግ ኮማንደር አወል ገልፀዋል፡፡
 

በድብቅ የሚከናወኑ መሰል ህገ ወጥ ተግባራት የሃገርን ኢኮኖሚ የሚያዳክሙና ጤናማ የገበያ ስርዓትን የሚጎዱ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው ኮማንደሩ አክለው የገለፁት፡፡