ባለፉት ሰባት ቀናት ግምታዊ ዋጋቸው ከ34 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ባለፉት ሰባት ቀናት በገቢና ወጭ ኮንትሮባንድ ግምታዊ ዋጋቸው 34 ሚሊየን 345 ሺህ 944 ሚሊየን ብር የሚገመት ዕቃ መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የገቢዎች ሚኒስቴር ባሉት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ኬላዎች አማካይነት በዚህ ሳምንት ኮንትሮባንድንና ህገወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዮ ስራዎችን መሰራታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዚህም ባለፉት ሰባት ቀናት በገቢ ኮንትሮባንድ 23 ሚሊየን 460 ሺህ 355 ብር የሚገመት ዕቃ መያዙን ገልጿል።

ከነዚህ መካከል አዳዲስ አልባሳት፣ ምግብና መጠጦች፣ ሲጋራና ትንባሆ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የጦር መሳሪያ እና የተሸከርካሪ መለዋወጫዎች ይገኙበታል።

እንዲሁም በሰባቱ ቀናት በወጪ ኮንትሮባንድ 10 ሚሊየን 885 ሺህ 589 ብር የሚገመት ዕቃ የተያዘ ሲሆን፥ ገንዘብ፣ ምግብና መጠጦች፣ ጫት እና ሌሎች ከተያዙት ዕቃዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

በሳምንቱ ውስጥ በህገ-ወጥ መልኩ ወደ ሀገር ሊገባ የነበረ 26 ሽጉጥ፣50 የክላሽ ጥይትና 43 የክላሽ ካዝና መያዙንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።