ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2011 ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆነች

በተጠናቀቀው ዓመት 2011 ኢትዮጵያ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች፡፡

ኢዋይ የተሰኘ አለምአቀፍ የፋይናንስ አማካሪ ተቋም ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ ሀገሪቱ በዚህ ዓመት ከ258 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሆነ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ችላለች፡፡

ይህ አሀዝም ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር አድርጓታል ነው ያለው፡፡

ኢትዮጵያን ተከትሎ ኬንያ 74 ሚሊየን ዶላር  ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ የቻለች ሀገር ሆናለች፡፡

ታንዛኒያ በበኩሏ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅሟ 36 ሚሊየን ዶላር በላይ በመድረሱ  ከቃጣናው የሶስተኝነት ደረጃን አሰጥቷታል፡፡

ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ዓመት በ29 ፕሮጀክቶች ከ16 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለች ሲሆን በአንፃሩ ኬንያ ከ64 ፕሮጀክቶች መፍጠር የቻለችው የስራ ዕድል 6 ሺህ ነው፡፡

ታንዛኒያ በምታንቀሳቅሳቸው 19 ፕሮጀክቶች ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት አመቺ አካባቢዎችን ማዘጋጀት መቻሏ እና ተወዳዳሪ የገበያ እድል መኖሩ ተመራጭ እንዳደረጋት  ነው በሪፖርቱ የተመለከተው፡፡

በተለይም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለውጪ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማመቻቸት በሩን ለኢንቨስትመንት ክፍት መድረጋቸው ለሀገሪቱ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

(ምንጭ፦ ዘ ሞኒተር)