የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እሴት መጨመር ላይ ትኩረት ይደረጋል ተባለ 

የኢንቨስትመንት ዘርፉን ዉጤታማ ለማድረግና  የዉጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የሚያስችል ስራዎችን  በጋራ ለመስራት የሚያሥችል የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ  ነዉ፡፡

የዱባይ የዲስፖራ ቢዝነስ ልዑክ ከኢትዮጵያ ባለሃብቶች ጋር እያካሄደ ያለው ምክክር የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የንግድ ትስስርን በማጠናከር በጋራ ለመስራት እንደሚያስችላቸዉ  የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ምስጋኑ አረጋ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከርና በሀገራቱ የሚገኙ ባለሃብቶች የልምድ ልውውጥ እንዲያካሂዱ በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር ዲኤታዉ አክለዉም በኢትዮጵያ በኩል የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ምርትን እሴት ጨምሮ ለመላክ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ነው የገለፁት፡፡

ምርቶችን በአይነትና በጥራት ማሳደግና  እሴት መጨመርም  የተሻለ ገቢን ከማስገኘት ባለፈ በርካታ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ እገዛው ላቅ ያለ መሆኑን  ሚኒስትር ድኤታው አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ሀገሪቱ ልምድ ልምድ ለመቅሰም ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኢትዮጵያና የተባበሩት አራብ ኢምሬቶች አምባሳደር ሙሃመድ ሳሌም አል ረሺድ በበኩላቸው ፤ የቢዝነስ ፎረሙ የንግድ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና ልምድና ተሞክሮዎችን ለመውሰድ ጥሩ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

“ወደ ብልፅግና የሚያመራውን ድልድይ መገንባት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው ይህ  ፎረም  ፤ የሃገራቱ ባለሃብቶች እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ በማድረግ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ይረዳል ተብሏል፡፡