11 ባለኮከብ ሆቴሎች በመዲናዋ ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ ከእቅድ በላይ የኢንቨስትመንት ፍስት እየታየባት መሆኗን እና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያስቀመጣቸውን ግቦች ማሳካት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ከሚሽን አስታወቀ።

የ11 ባለኮከብ ሆቴሎች ግንባታ ወደ ትግበራ እንዲገባ የከተማዋ ካቢኔ ውሳኔ ማሳለፉንም ገልጿል።

ሆቴሎቹን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚገነቧቸው እንደሆነም ኮሚሽነር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በተለይ ለአዲስ ዘመን ገልፀዋል፡፡

የእነዚህ ሆቴሎች ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትግበራ እንዲገባ ካቢኔው ውሳኔ ማሳለፉንና የካፒታል መጠናቸውም በጣም ብዙ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአንድ ሆቴል ብቻ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የካፒታል መጠን የቀረበበት ሁኔታ እንዳለም የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ይህም የሆቴል ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ2 ሺህ 500 በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ኮሚሽነሩ ጠቅሰው ፤ ወደ 40 ሺህ ኢንቨስተሮች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።