ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ርዕሰ መስተዳድሩ ከብቸና ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ብቸና ከተማ ላይ ከሕዝቡ ጋር እየተወያዩ ነው፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች እና ዛሬ የሚመረቀውን መንገድ በተመለከተ እየተወያዩ ሲሆን፣ በውይይታቸውም ኅብረተሰቡ መንገዱ የጥራት ችግር እንዳለበት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጥራት ችግሩን በተመለከተ የቀረበውን ሀሳብ ተቀብሎ በሥራ ተቋራጩ ወይም በሌላ መንገድ እንዲስተካከል እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡

ከባሕር ዳር- ዘማ ወንዝ- ፈለገ ብርሃን የሚዘልቀው የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ከደጀን- ሞጣ- ባሕር ዳር ያለውን አካባቢ ያስተሳስራል፡፡ ከባሕር ዳር – አዲስ አበባ በደብረ ማርቆስ በኩል የሚደረገውን ጉዞ በ80 ኪሎ ሜትር እንደሚያሳጥርም ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

መንገዱ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ትስስር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ታስቦ እንደተገነባ ተገልጿል፡፡

265 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መንገዱ ከውይይቱ በኋላ እንደሚመረቅ ይጠበቃል፡፡ ለሥራው 2 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወጪ እንደተደረገበት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ በ2005 ዓ.ም የተጀመረና የዲዛይን እና የጥራት ችግር ጥያቄዎች ይነሱበት ስለነበረም ማስተካከያ ለማድረግ በሚል በሥራው ላይ መጓተት ታይቶ ነበር፡፡
ዋና ዋና ሥራዎች መጠናቀቃቸውን፤ ሞጣ ከተማ ላይ 500 ሜትር የሚሆን የመንገዱ ግንባታ ክፍል እንደሚቀርና ይህንን ጨምሮ ሌሎች ማስተካከያዎች እንደሚከናወኑ አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡

ቀሪ የግንባታ እና የማስተካከያ ሥራዎች በባለሥልጣኑ እንደሚጠናቀቁ ታሳቢ ተደርጎ ከባሕር ዳር- ዘማ ወንዝ- ፈለገ ብርሃን የሚዘልቀው የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ዛሬ እንደሚመረቅ ይጠበቃል፡፡