ግማሽ ቢሊዮን ብር ወጭ የሚደረግበት የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ በባሕር ዳር ተጀመረ

ግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል፡፡

በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የሚገነባው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት 23 ሺህ ሜትር ኩብ /ከ30 ሺህ ሊትር/ በላይ የንጹሕ መጠጥ ውኃ በቀን ያመነጫል፡፡

ፕሮጀክቱ የከተማውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋን አሁን ካለበት 60 በመቶ ወደ 80 በመቶ ያሳድጋል የተባለው ሲሆን ፤ የከርሰ ምድር ውኃ ማበልጸግን፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን መገንባትንና ማስተላለፊያ መስመሮችን መዘርጋትን ያካትታል፡፡

የግንባታ ወጪው ከጃፓን መንግሥት በተገኘ ድጋፍ ነው የሚሸፈነው፡፡ የጃፓኑ ‹ኮኖኬ› ተቋራጭ ግንባታውን ያከናውናል፡፡

የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ይመር ሀብቴ ግንባታው በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡

ለጋሽ ሀገራት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን እያገዙ መሆኑን ያመለከቱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ 20 ከተሞችን እና 90 ወረዳዎችን ሊያግዝ የሚችል የአምስት ዓመት መርሀ ግብር ከዚህ ወር ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባም ነው ያስታወቁት፡፡

መርሀ ግብሩም በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በዩኒሴፍ፣ በኮሪያ እና በፊንላንድ መንግሥት ትብብር የሚደገፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዓለምነህ ታደሰ በበኩላቸው ፤ በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ማብቂያ አንድ ሰው በቀን 80 ሊትር ውኃ እንዲቀርብለት ቢታቀድም በቅርቡ በተሠራው ጥናት መሠረት 50 ሊትር ብቻ ነው እየቀረበ ያለው፡፡ ይህም የውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ በይፋ ሥራው የተጀመረው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የከተማውን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንደሚያሻሽለው የገለጹት ምክትል ከንቲባው ፤ ከተማ አስተዳድሩ በግንባታ ሂደቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጄንሲ ተወካይ ሃሩካ ናካጋዋ ኤጄንሲው ኢትዮጵያን በግብርናው ዘርፍ፣ በግል ኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት፣ በንጹሕ የመጠጥ ውኃ እና የኃይል አቅርቦት ዘርፎች ሀገራቸው እያገዘች መሆኑን መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡