ተመድ ለላሙ ፕሮጀክት ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት የላሙ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ።

በላሙ ወደብ ፕሮጀክት የአዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት (ኔፓድ)፣ ፅህፈት ቤት የኬንያ መንግስት ተወካዮች፣ በኬንያ ኤምባሲ እና የመንግስታቱ ድርጀት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፅህፈት ቤት ተወካዮች ውይይት አካሂደዋል፡፡

በትናንትናው እለት በናይሮቢ በተካሄደው በዚህ ውይይት የላሙ ፕሮጀክት በአፍሪካ መሪዎች የአህጉሩን ውህደት ያፋጥናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አስር ግዙፍ ቀጠናዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛው መሆኑ ተገልጿል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ አዴይንካ አዴዬሚ ፕሮጀክቱ ኢኮኖሚያዊ ልማትን ከማረጋገጥ ባሻገር ቀጠናዊ ሰላምን ለማምጣት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ባለቤቶች የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ለስራዎቹ መጠናቀቅ ተቋማዊ አቅማቸውን ማጠናከር እና ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የተጎራባች ሕዝቦችን በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማምጣት የሚዘረጋውን የላሙ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ከኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኔፓድ እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ከመሳሰሉ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር ተባብራ ትሰራለች ብለዋል።

የላሙ ወደብ ብሮጀክት የቀጠናውን ብቻ ሳይሆን የአህጉሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ትስስሮሽ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣትን ራዕዩ አድርጎ የሚገነባ ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አጎራባች አርብቶ አደር ማህበረሰብ ኑሮ በዘላቂነት የሚለውጥ በመሆኑ ግጭቶችን ለማስወገድ እንደሚረዳ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የላሙ ፕሮጀክት አካል የሆነው አንደኛው የመርከቦች ማቆያ በቅርቡ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።