በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከግብጽ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በግንባታው ሂደት ላይ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር ተገለጸ

ከሰሞኑ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ ጋር የተፈተረዉ አለመግባባት በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማይፈጥር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከሰሞኑ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከግብጽ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በግደቡ ግንባታ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማይፈጥር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል ፡፡

ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የተዉጣጣዉ 15 ሳይንቲስቶችን ያካተተዉ ብሔራዊ ገለልተኛ ሳይንሳዊ ቡድን ያቀረበዉን ሃሳብ የሚፃረር አካሄድን ግብፅ እየተከተለች መሆኑ ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ተመልክቷል።

ግብጽ የያዘችው አቋም የኢትዮጵያን ህልዉና አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ በመገኘቱ አለመግባባት መፈጠሩን አስታውሰው፤ይሁን እንጂ የተፈጠረው አለመግባባት በግድቡ ግንባታ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የማይፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሳይንቲሰቶቹ ቡድን የሚያቀርበዉን ሀሳብ ተቀባይነት እንዲኖረውና ባለፉት 7 ዓመታት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የነበረዉ የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትሻለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው፤ ከግድቡ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ የተፋሰሱ ሀገራት አካሄዶች ተቀባይነት አይኖራቸዉም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለና ጥቅሞቿን በጠበቀ መልኩ በአባይ ወንዝ መጠቀሟን ትቀጥላለችም ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለዉም ባሳለፍነዉ ማክሰኞ በተጀመረዉ 74ኛዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግና ይህም ጥቅሞቿን ባስከበረ መልኩ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በዘንድሮዉ ጉባኤ በምክትል ፕሬዝደንትነት መመረጧ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑን ያነሱት አቶ ነቢያ፤ ጉባኤዉ የኢትዮጵያን ጥቅሞች ያስጠበቀ እንዲሆን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡