በግንባታ ጥራትና አፈጻጸም ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው

የግንባታዎች ጥራትና አፈጻጸም ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሁለት የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በተካሄደ ሙከራ ጥራትን በማሻሻል፣ የባለ ድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከርና በሌሎችም ለውጦች ተገኝተዋል ተብሏል።

ኢንስቲትዩቱ ‘አውቶ ዴስክ’ ከተሰኘ የአሜሪካ ሶፍትዌር አምራች ድርጅት ጋር በመተባበር የሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ሲያካሂድ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ አስመሮም ታደሰ እንደተናገሩት፤ ግንባታዎችን በጥራት፣ በጊዜና ወጪን በቆጠበ መልኩ ማከናወን የሚያስችል የህንጻ መረጃ ሞዴል ሶፍትዌር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

የቴክኖሎጂው ሶፍትዌርና አስፈላጊ መሳሪያዎች ግዢ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መፈጸሙን ተናግረዋል።

የፕሮጀክት አስተዳደር ብቃት አነስተኛ መሆን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ያለመጠቀም፣ የጥራት መጓደልና ሌሎችም ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ዋነኛ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።

የግንባታ ወጪዎች ከተመደበው በጀት ጋር ያላቸው ልዩነት ከፍተኛ መሆን፣ የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ፣ በግንባታ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ አለመለየትና መፍትሄዎችን ያለማዘጋጀት፣ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ብቃት ማነስንም እንዲሁ።

በመሆኑም ከፕሮጀክቶች ዲዛይንና እቅድ አወጣጥ እስከ አፈጻጸም ባሉት ደረጃዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል።

የህንጻ መረጃ ሞዴል ሶፍትዌር ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሁለት የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ሙከራ የተደረገ ሲሆን በተያዘው ዓመት ሶስተኛ ፕሮጀክት ላይ ይተገበራል።

በሙከራ ፕሮጀክቶቹም በግንባታ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቀነስ፣ ጥራት በማሻሻል፣ የባለ ድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከሩ በኩል ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም ለ18 ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን፣ በቀጣይም ከሶፍትዌር ፈጣሪው ድርጅት ጋር በመሆን ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ በቅንጅት እንዲተገበር ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንና በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።