ባለስልጣኑ በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ያለውን የኪሎ ሜትር ገደብ ለአጭር ጊዜ ብቻ አነሳ

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ወቅት ተማሪዎችን የትራንስፖርት እጥረት ችግር እንዳያጋጥማቸው በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ያለውን የኪሎ ሜትር ገደብ ለአጭር ጊዜ ብቻ አንስቷል፡፡

በሀገሪቱ በትምህርት መስኩ መጠነ ሰፊ የማስፋፋት ስራ እየተሠራ በመሆኑ የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች መከፈትና የተማሪ ቅበላ መጠን እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ጥሪ የሚያደርጉበት ወቅት የተለያዩ ህዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚደራረቡበት ወቅት በመሆኑ የትራንስፖርት አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ባለስልጣኑ ጠቅሷል፡፡

ስለሆነም አቅርቦቱን ለማሻሻልና የተማሪዎችን እንግልት ለመቀነስ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ ተሽከርካሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማጓጓዝ ብቻ ከመስከረም 10 ቀን 2012 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ብቻ በኪሎ ሜትር ሳይገደቡ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ብሏል፡፡

በዚሁ መሰረት የክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ተቋማት በመናኸሪያዎች ሠራተኞችን በመመደብ ተማሪዎች ሳያቆራርጡ በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚደርሱበትን ትራንስፖርት በማቀናጀት ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹና የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካልም ጉዳዩን አውቆ ትብብር እንዲያደርግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተሽከርካሪዎች ላይ የነበረው የኪሎ ሜትር ገደብ ለአነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች እስከ 150 ኪሎ ሜትር፣ ለመለስተኛ ከ150 እስከ 250 ኪሎ ሜትርና ለአገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡