የህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለእረፍት በቀንና በሌሊት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከምንግዜም በላይ በቀንና በሌሊት ያለምንም እረፍት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቆሟል በሚል የሚሰራጨው ፕሮፖጋንዳ ከእውነት የራቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ ገለፁ።

በየጊዜው ግድቡ ቆሟል በሚል በግብፅና በተለያዩ አፍራሽ ኃይሎች የሚሰራጨውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመያዝ አሉታዊ መልዕክት የሚያስተላልፉ አካላትን ውሸትና ሴራ የምናጋልጠው ግንባታውን በተግባር በማፋጠን ብቻ መሆኑን በመግለጽ፤ አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ ከምንግዜም በላይ በቀንና ሌሊት ያለምንም እረፍት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከግንባታው ጋር ተያይዞ የሚናፈሰው ወሬም ምንም እውነት የሌለውና ግብፅ መቼውንም ቢሆን ለኢትዮጵያ አስባ የምታቀርበው ሃሳብ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል በማለት ተናግረዋል።

ይልቁንም የግድቡን ግንባታ ማስቆም እንደማትችል የተረዳችው ግብፅ አሁን ላይ አካሄዷን በመቀየር ግድቡ በረጅም ጊዜ እንዲሞላና ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ ሲገባ ኦፕሬሽኑ እንዴት ይካሄድ የሚሉ፤ ፍላጎቶቿን ያሳኩልኛል ያለቻቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮሯን ዶ/ር አብርሃም ጠቁመዋል፡፡

ከሰሞኑ በተደረገው የሶስትዮሽ ውይይት ላይም የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ፍሰት፤ የአስዋን ግድብ በሚኖረው የውሃ መጠን ላይ እንዲመሰረት ግብፅ ያቀረበችው ምክረ ሃሳብ የኢትዮጵያን የመልማት ጥያቄና ሉዓላዊ መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀዋል፡፡

ግድቡ የምንገነባው ተገንብቷል ለማለት ሳይሆን ሀገሪቱ የምትፈልገውን ኃይል ለማሟላት በዓመት በአማካይ 15670 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ጉልህ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ በመሆኑ ይህን መብታችንን ለድርደር አይቀርብም ብለዋል::

ከኃይል ማመንጨት አቅም ጋር ተያይዞም ከግብፅ ጋር በመደራደር የግድቡ የማመንጨት አቅም እንዲቀንስ ተደርጓል በሚል የተናፈሰው ዘገባም ከእውነት የራቀ እና አሉባልታ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግድቡ መያዝ የሚችለው ውሃንም ሆነ የማመንጨት አቅም መቀየር የሚቻልበት እድል እንደሌለ ገልጸዋል።

የአንድ ግድብ የማመንጨት አቅም በመሰረቱ የሚወሰነው ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠን እና ውሃው ከተርባይን ማእከል በሚኖረው ከፍታ ልዩነት እንጂ በሚተከሉት ተርባይኖች ብዛትና መጠን ብቻ አለመሆኑንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ከግብፅ በመደራደር የጀነሬተር ወይም ተርባይን ቁጥሩ ተቀንሷል የሚባል አሉባልታ የሚያናፍሱ አካላት የውሃ ኃይል ማመንጫ እንዴት እንደሚሰራ ግንዛቤ የሌላቸው አልያም ሆን ብለው ሰዎችን ለማደናገር የሚሞክሩ ናቸው ብለዋል፡፡

(ምንጭ:- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል)