አቶ ገዱ ከፊንላንድና ኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኒውዮርክ እየተካሄደ ካለው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከፊንላንድና ኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ገዱ ከፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ፔካ ሃቪስቶ ጋር ባደረጉት ምክክር ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሠላም ለማስፈን እያደረገች ያለውን ጥረት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚሁ ወቅት አድንቀዋል፡፡

በተለይም በቅርቡ በሱዳን ስምምነት ለማምጣት ኢትዮጵያና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለተጫወቱት ዲፕሎማሲያዊ ሚና አድናቆታቸውን መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ለሠላም አበክራ እንደምትሰራና በአፍሪካ ቀንድ የሚፈጠር ሠላምም ቀጣናውን የልማትና የብልፅግና አካባቢ ለማድረግ ለሚሠሩ ስራዎች ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ ቀጣናዊ ሠላም ለማምጣት በጋራ ከመስራት ባሻገር በሁለትዮሽ ግንኘነታቸው ፊንላንድ በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር እንደምትሰራ መግባባት ላይ መድረሳቸውም ተመላክቷል።

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬትኖ ማርሱዲ ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገራቱ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎቻቸው ያለ ቪዛ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲኖራቸው መስራት እንደሚያስፈልግ አቶ ገዱ ተናግረዋል።