አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በታኅሣሥ መጨረሻ ለባለሀብቶች ይተላለፋሉ

አራት ክልሎች በመገንባት ላይ የሚገኙ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በታኅሣሥ መጨረሻ ለባለሀብቶች እንደሚተላለፉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

«ክልሎች ባልተጠና መልኩ ሕገወጥ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ መጀመራቸውም አስግቶኛል››ብሏል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አያልነህ አባዋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ግብርናውን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ከጥምረቱ ፍሬ ተጠቃሚ ለመሆን በ2009 ዓ.ም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተጀምሯል።

ለዚህም 17 ቀጣናዎች የተለዩ ሲሆን፤ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ የጥሬ ዕቃዎች ምርት መገኛ መሆናቸውን መሠረት በማድረግ የመጀመሪያዎቹ ፓርኮች ግንባታ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልል ተግባራዊ ተደርጓል።

ባለፉት ዓመታትም ፓርኮቹን ገንብቶ ሥራ ለማስጀመር የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ አያልነህ፤ በአሁኑ ወቅት ፓርኮቹን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ መሠረታዊ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውንና በመጪው ታኅሣሥ መጨረሻ ለባለሀብቶች እንደሚተላለፉም ጠቁመዋል።

አቶ አያልነህ በፓርኮቹ ውስጥ የሚሰማሩ ብቃት ያላቸው ባለሀብቶችን በመመልመል ረገድ ጥናትና የሌሎች አገራት ተሞክሮ የመቃኘት ተግባር በጥንቃቄና በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ወደ ፓርኮቹ ለመግባት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ተመዝግበው እየተጠባበቁ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ አያልነህ፤ ቀደም ብለው ወደ ሥራ በመግባት ማምረትና ግንባታ የጀመሩ ስለመኖራቸውም አስታውቀዋል።

የፓርኮቹ ግንባታ የተጀመረው በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፤ በበጀት እጥረት የትግራይ ክልል ወደ ኋላ መቅረቱንና አንዳንድ ግንባታዎች አለመጀመራቸውንም አብራርተዋል።

‹‹የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ዋነኛ ፈተና የኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ነው›› ያሉት አቶ አያልነህ፣ በአሁኑ ወቅት በፓርኮቹ ሥራ የጀመሩ ባለሀብቶችም ቢሆኑ  በእራሳቸው አቅም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ወስነው የገቡበት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ድርድር ተካሂዶ አቅርቦቱን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ ግን ልዩ ትኩረት እንደሚሻው አስገንዝበዋል።

‹‹ከኃይል አቅርቦቱ በተጓዳኝ በአሁኑ ወቅት ከፌዴራል መንግሥት እውቅና ውጪ አንዳንድ ክልሎች የፓርኮች ግንባታ እያከናወኑ መሆናቸው በጣም ያሳስበናል›› ያሉት አቶ አያልነህ፣ አንዳንዶቹ ክልሎችም ተጨማሪ ፓርክ ለመገንባት ቦታ ከመምረጥ ባለፈ በልማቱ ለሚነሱ አርሶ አደሮች ካሳ ከፍለው መጨረሳቸውን አስታውቀዋል።