ኢትዮጵያ ከሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በትኩረት ይሰራል ተባለ

በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፍረነስ በነሀሴ ወር መደረጉ ይታወሳል፡፡

የዚሁ ጅምር አካል የሆነው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት አለምአቀፍ ጉባኤ እየተካሄደ  ይገኛል፡፡

ጉባኤው በዋናነት በአፍሪካ የሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም መፍትሄዎች ላይ በማተኮር ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው አፍሪካ ያላትን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝምና ተያያዥ ሃብቶች በሚገባ እንዳልተጠቀመችበት አንስተው ይህን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በመንግስት በኩል በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች፣ የተለያዩ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብቶች መያዟን ተከትሎ የቱሪዝም መናኸሪያ ብትሆንም በአግባቡ እየተጠቀመችበት አለመሆኑን አንስተዋል።

በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሰረት አንድ ቱሪስት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ በአማካይ እስከ 10 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡

ከዝቅተኛው ስፍራ ዳሎል እስከ ራስ ዳሽን ባለው አስር አይነት የተለያየ ስነ ምህዳር እንዳላት የሚነገረው ኢትዮጵያ 11 ቅርሶቿን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፤ የሳይንስና ባህል ተቋም አስመዝግባለች፡፡

ዘርፉ ለኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ ለማጎልበት የሰለጠነ የሰው ሀይል በበቂ ሁኔታ አለመኖር፤ ወጥነት ያለው አስራራ አለመዘርጋትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆኑ ተግዳሮት እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡

እስከ ነገ መስከረም 14፣ 2012 ዓ.ም በሚቆየው ጉባኤ ከ52 ሀገራት የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተካፈሉ ይገኛል፡፡