የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑ ተገለጸ

በደቡብ ክልል የሚገኘው የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብሩ ወልዴ ለዋልታ እንደተናገሩት የፓርኩ ግንባታን በማፋጠን የአስተዳደር ህንፃዎችን ጨምሮ በዚህ ዓመት ሊገነቡ ከታቀዱት 11 የፋብሪካ ሼዶች አስካሁን አራቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል፡፡

በፓርኩ ለመሳተፍ ከተመዘገቡ ባለሀብቶች ማካከል ከፓርኩ ውጭ በጊዜያዊነት በተዘጋጀላቸው ቦታዎች የማር በማምረት ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ብሩ፣ ሳንቫዶ የተባለ የሆላንድ ኩባንያ በፓርኩ ቅጥር ግቢ የተገነባለትን አንድ ሼድ ተጠቅሞ አቮካዶ እና ዘይቱን ማቀነባበር ጀምሯል፡፡ አንድ የጣሊያን ኩባንያም ቡናን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በማቀነባበር ስራ ላይ ለመሳተፍ ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል፡፡

ጥሬ ዕቃዎችን ለፋብሪካው የሚያቀርቡት አርሶአደሮች የክህሎት ስልጠናዎች የሚያገኙበትና የምርት ማስረከቢያ ቦታ ሆኖ የሚያገለግሉ ማዕከላት በበንሳ ደላ እና የይርጋጨፌ ከተሞች በእያንዳንዳቸው 10 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነቡ ነው፡፡ በፓርኩ ውስጥ ለውስጥና ፓርኩን ከዋና መንገዶች ላይ ለማገናኘትም የ13 ኪሎሜትር የአስፋልት መንገድ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡  

በቡና፣ ፍራፍሬና ወተት ማቀነባር ዘርፎች አተኩሮ ይሰራል የተባለው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርክ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ 400 ባለይ ለሚሆኑ አርሶአደሮች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡

በ2010 ግንባታው የተጀመረው ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 152 የማምረቻ ፋብሪካዎች የሚገነቡለት ሼዶች ይኖረዋል፡፡ 300 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ 6 ቢሊየን ብር ገደማ ይፈጃል ተብሏል፡፡

በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ይርጋለም ከተማ እየተገነባ ያለው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮፕሮሰሲንግ ፓርክ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትግራይ በከር፣ በኦሮሚያ ቡልቡላና በአማራ ክልል ቡሬ እየተገነቡ ካሉት የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች አንዱ ነው፡፡