የቱሪዝም ኃብት በኢኮኖሚ ልማት ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኃብትን ለስራ እድል ፈጠራና የኢኮኖሚ ልማት ጉልህ ሚና እንዲኖረው ለማድርግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የቱሪዝም ቀን በዓለም ለ40ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በስፍራው ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የቱሪዝም ዘርፍ ለአገር ልማት ወሳኝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው።

የቱሪዝም መዳረሻዎች መሰረተ ልማታቸው ምቹ እንዲሆንና የአገልግሎት አሰጣቱ አስደሳችና ቀልጣፋ እንዲሆን መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ ሳይሆን በእንግዳ ተቀባይ ሕዝቧ በታሪኳ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቷ ለቱሪስት መስህብነት ከቀዳሚ አገሮች ተርታ ያሰልፏታል።

ሆኖም ይህንን እምቅ ሃብቷን እስካሁን በአግባቡ እየተጠቀመችበት አለመሆኑ ይነገራል።

በቀጣይ ከዘርፉ የሚመነጨው ሃብት ለአገር ልማትና ለስራ እድል ፈጠራ  አይነተኛ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል በትብብር መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ለዚህም ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘርፉ ስኬታማነት ሰላሟ ተጠብቆ ለጎብኝዎች ምቹና ተመራጭ አገር ለመፍጠር ርብርብ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ እንዳሉትም ቱሪዝም ትልቅ የገቢ ምንጭና የበርካቶች ስራ እድል ማግኛ ዘርፍ እንዲሆን ስትራቴጂክ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ ነው።

ድሬዳዋ ያሏት እምቅ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም የከተማዋ አይነተኛ የገቢ ምንጭ እንዲሆን የተለያዩ ተግበራት እየተከናወኑ መሆኑም ታውቋል።

በዚሁ ዙሪያ በጥናት ላይ በመመስረት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም አቶ ሙራድ ተናግረዋል።

ቱሪዝም ከሰላምና ደህንነት ጋር ቀጥታ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ከማህበረሰቡ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የፀጥታ መዋቅርና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ቀን “ለስራ እድል ፈጠራና ለተሻለ ህይወት በሚል መሪ ሃሳብ” በድሬዳዋ ከተማ በመከበር ላይ ይገኛል።

እለቱን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ከመጎብኘት በተጨማሪ በስፖርታዊ ውድድሮች ለማክበር መርሃ ግብር ተይዞለታል።

የዓለም የቱሪዝም ቀን በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን የሚከበር ሲሆን ኢትዮጵያም 157 አባል አገሮችን ያቀፈው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት አባል መሆኗ ይታወቃል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)