ኢትዮጵያ በ40ኛው አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ በሚገኘው 40ኛው አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያም በትራንስፖርት ሚንስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን በመወከል እየተሳተፈች ነው፡፡

አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ዘንደሮ 75ኛ አመቱን አስቆጥሯል፡፡

በዘንደሮው ጉባኤ ከመስራቾቹ መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በትራንስፖርት ሚንስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊ ሞገስ የተወከለች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያበረከተች ላለው አስተዋጽኦ በጉባኤው ተወስቷል፡፡

በጉባኤው ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል ሬቨኑ ፓሴንጀር ሬት (IRP) 90 በመቶ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ 36 የአለም ሃገራት ውስጥ አንዷና መሆኗም ተገልጿል፡፡

በአፍሪካም በቀዳሚነት ደረጃ የምትገኝ መሆኗ በጉባኤው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ወ/ሮ ዳግማዊት በማህበራዊ ድረገፅ ላይ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስትሯ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኳታር ትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ጃሲም ቢን ሳይፍ አል ሱልታኒ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በዚህም ሀገራቱ በትራንስፖርትና በሲቪል አቪዬሽን ዘርፋ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።