የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ

በቻይና መንግሥት ድጋፍ የሚገነባው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

አጠቃላይ 56 ኪ.ሜ ከሚሆነው የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ በቻይና መንግሥት የሚደገፈው 12 ኪ.ሜ ፕሮጀክት ነው።

የ12 ኪ.ሜ ፕሮጀክቱ በሁለት ዙር የሚሠራ ሲሆን አሁን የተጀመረው የመጀመሪያው ዙር ፕሮጀክት በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሏል። ሁለተኛው ዙር ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ነው የተነገረው።

ፕሮጀክቱ አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብ እና ማራኪ በማድረግ ለመዝናናት እና ለቱሪዝም ምቹ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እና ለአፍሪካም አርአያነት ያለው ሥራ እንደሚሠራ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ተናግረዋል።

የቻይና መንግሥት የሚያስገነባው ፕሮጀክት የትምህርት፣ የኮንሰርት ማቅረቢያ፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና ሰው ሠራሽ ሐይቆች ያሉት እና ዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን ስለዚሁ ፕሮጀክት በቪዲዮ የቀረበው ናሙና ያመለክታል።