በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ በመተካቱ ሂደት ላይ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ በመተካቱ ሂደት ላይ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የታክሲ አገልግሎት (ኤታስ) ከሚሰጡ 13 ተቋማት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የኤታስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲከተሉት ባወጣው መመሪያ ዙሪያ እና የትራንስፖርት ሴክተሩን በዘላቂነት ዘመናዊ ለማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ከኤታስ እና ሶፍትዌር ማበልፀጊያ ተቋማት ጋር ምክክር ተካሂዷል፡፡

የኤታስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ በከተማ አስተዳደሩ ረቆ በቅርቡ ይፋ የሆነው መመሪያ ቴክኖሎጂው ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደሌለው በመግለፅ፤ ህጉን እንደማይቃወሙ እና ለተፈፃሚነቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት አሰጣጥ በከተማዋ ውስጥ እንዲስፋፋ ፍላጎቱ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የሚረዱ ሌሎች ተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን ለሚያመጡ በራቸው ክፍት መሆኑንም ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይነትም የከተማ አስተዳደሩ የተቀላጠፈ እና ህዝቡን የሚጠቅም መመሪያ ቀርጾ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

የኤታስ ተቋሞቹም በከተማዋ ውስጥ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎች ያረጁ በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ተሽከርካሪዎቹን በአዲስ በመተካቱ ሂደት ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ፅህፈት ቤት)