የአዲስ አበባ ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ እሁድ ይጀምራል

የአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ህንጻ ግንባታ ሊጀመር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የግንባታ ማስጀመሪያ ስነስርዓቱ እሁድ ከጠዋቱ 2:30 ሰዓት ጀምሮ የከተማዋና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ይከናወናል፡፡

ህንጻው ከመሬት ስር የሚገነቡ አራት ወለሎች የሚኖሩት ሲሆን፤ ከትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል በተጨማሪ መረጃ ማደራጃ ክፍሎች፣ የወንጀልና የአደጋ መከላከያ መረጃ ቢሮዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ያካትታል፡፡

ፕሮጀክቱ ከመሬት ስር የሚጠናቀቅ ሲሆን ከመሬት በላይ ለአረንጓዴ ልማት እንደሚውል ተገልጿል፡፡

በማዕከሉ በሚገጠሙ ግዙፍ የቴሌቪዥን ስክሪኖች አማካኝነት የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ በቀጥታ ማየትና መቆጣጠር የሚቻል በመሆኑ የከተማዋን የትራፊክ ቁጥጥር ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡

ማዕከሉ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ከሚያበረክተው አስተዋጽዖ በተጨማሪ በከተማዋ የጸጥታ፣ የአደጋ ቁጥጥርና የወንጀል ቁጥጥር ስራዎችም ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል ተብሏል፡፡

በማዕከሉ ውስጥ የትራፊክ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የትራፊክ መብራቶችን የቆይታ ጊዜ እንደ ትራፊክ ፍሰቱ መጠን የመቀያየርና ልዩ ልዩ የትራፊክ ፍሰት ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ስራም ይከናወንበታል፡፡

በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የመንገዶችን የትራፊክ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁና አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ መረጃ የመስጠት፣ የትራፊክ ህጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን የመለየት እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት፣ የአደጋ እና የደህንነት መረጃዎች ወደሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ተቋማት በጊዜው እንዲተላለፉ ማድረግ ያስችላል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ ሙሉ ወጪ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን ከአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡

በዕለቱ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ህንጻ ግንባታም እንደሚጀመር ተጠቁሟል፡፡