የሕዳሴው ግድብ የማመንጨት አቅም እንደማይቀንስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅሙ ሊቀንስ ነው ተብሎ እየተነገረ ያለው መረጃ ትክክል አለመሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በ16 ተርባይኖች በዓመት በአማካይ 15 ሺህ 670 ጊጋዋት በሰዓት ኃይል የማመንጨት ዕቅድ ተይዞ ወደ ግንባታ መገባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይገልፃል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ሰዓት አማራጭ ጥናቶች ከተደረጉ በኋላ የተርባይኖቹን ቁጥር በመቀነስ እና የማመንጨት አቅማቸውን በመጨመር ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መሥራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

በዚህም ቀደም ሲል ከታቀዱት 16 ተርባይኖች አሁን 3ቱ መቀነሳቸውን ነው የገለጹት።
የአንድ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ የማመንጨት አቅም የሚወሰነው ግድቡ በሚይዘው የውኃ መጠን እና ውኃው ከተርባይን ማዕከል በሚኖረው ከፍታ ላይ እንጂ በተርባይኖች ብዛት አለመሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

የተርባይኖች ቁጥር በጨመረ ቁጥር የሚጨምረው ኃይል እንደማይኖርም አስምረውበታል።

በዚህም 16 የነበሩ ተርባይኖች ወደ 13 በማድረግ በዓመት የሚጠበቀውን 15 ሺህ 670 ጊጋዋት በሰዓት የማመንጨት አቅም በመፍጠር ቀድሞ በነበረው መንገድ ያንኑ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል መደምደሚያ ላይ ተደርሶ እየተሠራ መሆኑንም ኢንጅነር ክፍሌ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ሞገስ መኮነን በበኩላቸው “ግብፆች ከዚህ በፊት በነበረ ድርድራቸው የግድቡን ከፍታ ቀንሱ፤ ውኃ የሚይዘውን ጊዜ አራዝሙ” የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ እና ተፅዕኖ ለማሳደር ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው ከዚህ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩት መረጃዎች ትክክል አለመሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ግድቡ የሚይዘው የውኃ መጠን፣ ከፍታው እና የማመንጨት አቅሙ ሳይቀንስ በ13 ተርባይኖች ውጤታማ በሆነ መልኩ ቀድሞ ማመንጨት የታሰበውን ኃይል ለማመንጨት በሚያስችል ሁኔታ እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአሁኑ ጊዜም የግድቡ ግንባታ 68.5 በመቶ ላይ መድረሱን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡