የዓለም የሜቲሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ ሊከፍት ነው

የዓለም የሜቲሮሎጂ ድርጅት (WMO) የአፍሪካ ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ ሊከፍት መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ህይወት ሞሲሳ የዓለም የሜቲሮሎጂ ድርጅት (WMO) ሴክሪተሪ ጀነራል ፒተሪ ታላስን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ወ/ሮ ህይወት በውይታቸው የዓለም የሜቲሮሎጂ ድርጅት (WMO) የአፍሪካ ጽ/ቤቱን በይፋ ለማስጀመር መወሰኑ እንዳስደሰታቸውና በጋራ ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ሴክሪተሪ ጀነራል ፒተሪ ታላሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ እያስመዘገበች ያለችው እድገት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ በመሆኑ ሀገሪቱን ተመራጭ ካደረጓት ጉዳዮች መካከል ዋንኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በአዲስ አበባ ጽ/ቤቱን መክፈቱ የኢትዮጵያ አቭዬሽን ድርጅት እየያከናወነ ለሚገኘው ድህንነቱን የጠበቀ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጨማሪ አቅም ከመሆኑም በላይ ለቴክኒካዊ ድጋፍና ጥራት ያለውና ተአማኒ መረጃ ከመስጠት አኳያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡

ሴክሪተሪ ጀነራሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰላም የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ለወ/ሮ ህይወት መግለፃቸውን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡