ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ከአለም የምግብ ልማት ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተርና ከአለምአቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአለም የምግብ ልማት ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌይ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በዘላቂ ልማት ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን ተቋሙ ከመንግሥት ጋር በቀጣይ የበለጠ ተቀናጅቶ በመስራት ረገድ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከዚህ ባለፈም ተቋሙ በቀጣይ ከመንግስት ጋር የበለጠ ተቀናጅቶ መስራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በጣልያን ቆይታቸው ከኢፋድ [IFAD] ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሁንግቦ ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡

በሃገሪቱ የተጀመሩ የመስኖ ሃብት ልማት እና የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን የማሳደግ እንቅስቃሴ ዙሪያ ተወያይተዋል።

ተቋሙ በሃገሪቱ በግብርና ልማት ዙሪያ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች እንደሚያጠናክር እና በቀጣይ የድጋፍ ፕሮግራሞች በጥናት አስደግፎ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።