የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ44 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተገለጸ

የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 44.45 ሚሊዮን መድረሱን እና በዚህም የዕቅዱን 99.5 በመቶ መፈጸሙን ቴሌኮሙ አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የመስሪያ ቤቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ስራ አፈፃጸም በሚመለከት ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በሩብ ዓመቱ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10.4 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተጠቅሷል።

ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ሲያደርግ መቆየቱ ተነግሯል።

እንደ ኢቢሲ ዘገባ ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 10.1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል።

በዚህም ድርጅቱ የእቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉን የገለጹት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 56 በመቶው ከድምጽ አገልግሎት 29 በመቶው ደግሞ ከሞባይል ዳታ የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 41.1 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናገሩት።

የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።