20ኛው የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀመረ

አዲስ አባባ፤ ጥር 18 ቀን 2004 (ዋኢማ) – የአፍሪካ ህብረት ያስቀመጣቸው ግቦች እንዲሳኩ ለእርስ በእርስም ሆነ ክፍለ አህጉራዊ ግንኙነቶች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበርዣን ፒንግ ገለፁ፡፡

ዣን ፒንግ 20ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክርቤት ስብሰባ በተጀመረበት ወቅት ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም እያደረገች ያለችውን አስተዋፅኦም አድንቀዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወይንም የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነትን ሊያሳድጉ ይገባል የሚለውን ጉዳይ መርህ አድርጎ የሚመክረው 18ኛው የመሪዎች ጉባኤ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከሚካሄዱ ጉባኤዎች ዋነኛው ነው፡፡ ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡

በስብሰባው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የህብረቱ ኮሚሽነር ዶክተር ዣንፒንግ እንዳሉት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማስፈን በሰሜን አፍሪካ የተካሄዱ አብዮቶች መልካም የሆኑ ዘላቂ ለውጥእንዲያመጡ በብሄራዊ እርቅን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ የህብረቱ አባል ሀገራት ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ በሱማሊያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የሽግግር መንግስቱ ለመደገፍ እየተደረገ ባለው ጥረት የሰላም አስከባሪ በመላክ የተባበሩ ጅቡቲ ፣ ብሩንዲና ሩዋንዳን ዣን ፒንግአመስግነዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢጋድ መሪነት ለአካባቢው ሰላም እየደረገችው ያለችውን አስተዋጽኦም የኮሚሽንኑ ሊቀመንበር አድንቀዋል፡፡

ዶክተር ዣን ፒንግ እንዳሉት የአፍሪካ ህብረት የሚያልማቸው ግቦች እንዲሳኩ የህብረቱ አባል ሀገራት የእርስ በርስ እና ክልላዊ ግንኙነት ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ አብዱላሂ ጃኔ በበኩላቸው ብዙ ሀገራት በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሲዳክሩ አፍሪካ በአንጻራዊነት የተሻለ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ማስመዝገቧን ነው የገለጹት።

ምንም እንኳ በሰሜን አፍሪካ የነበረው አለመረጋጋት በአጠቃላይ አህጉሪቱ ዕድገት ላይ የራሱ ተፅእኖ ቢያሳድርም። አብዱላሂ ጃኔ በአህጉሪቱ ያለውን ዕድገት ለማስቀጠል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሉዋቸውን ጉዳዮችምገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ሁነኛ አጋር በሆነው የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ላይ የሚታየው የምጣኔ ሀብት መዋዠቅ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በአፍሪካ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡በተለይ በቱሪዝም በኢንቨስትመንት በንግድና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚላክ ገንዘብ ላይ።

ይሁን እንጂ አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ እንደ ብራዚል ቻይና ህንድ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በማጠናከር ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እንደምትችል ነው ያብራሩት ፡፡

በአለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ እያራመደችው ያለችው ወጥ አቋም ተጠቃሚነቷን ከፍ እያደረገው መምጣቱንም ገልፀዋል፡፡