የኤርትራ ሚዲያ አጀንዳ ኤርትራውያን የሌሎች አገራትን ችግር እንጂ መልካም ነገር እንዳያዩ ማድረግ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 10 (ዋኢማ) – የኤርትራ ሚዲያ አጀንዳ በሌሎች አገራት ለሚፈጠሩ ችግሮች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ኤርትራውያን የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳሉ አድርገው እንዲያስቡና በሌላው ዓለም የተዛባ አመለካከት እንዲይዙ ማድረግ መሆኑን ጋዜኛኛ ሰናይ ገ/መድህን አስታወቀ፡፡

ኤርትራ እየፈረሰች፣  እየወደመችና  ምጣኔ ሃብቷ  እየተሸመደመደ ባለችበት በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ሚዲያ አገሪቱ በጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለች ለማስመሰል እየሰራ መሆኑን ጋዜጠኛ ሰናይ ገብረ መድህን ተናግሯል፡፡

ጋዜጠኛው ለዋልታ እንገለጸው የኤርትራ ህዝብ ሌሎች አማራጮችን እንዳይመለከትና በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያይ ማድረግ የሚዲያው ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡

የሌሎች አገራትን መጥፎ  ገጽታ በሰፊው በማቅረብ ኤርትራ  የተሻለች አገር አስመስሎ  ማሳመን  የሚዲያው የእለት ተለት ተግባር ነው ብሏል ጋዜጠኛው፡፡

እንደ ሰናይ ገብረ መድህን ገለጻ የሚዲያው ባህሪ የመነጨው ከአምባገነኑ የኢሳያስ መንግስት ባህሪ በመሆኑ የህዝቡን ማህበራዊ ጉደያች የሚቀርብበት  ሁኔታ የለም፡፡

በኤርትራ ሚዲያ ስለ ፖለቲካ ምርጫ በጎ ነገር አይነሳም፣ በኤርትራ ሚዲያ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር በጎ ነገር አይነሳም፣ ስለግሎባላይዜሽን በጎነት አይነሳም፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ስለሚደረጉ በጋራ የመኖር በነፃነት የመኖር ጉዳይ አይነሳም፣ ስለ ነፃ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አይነሳም” ብሏል

ለአስራ አራት ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገለው ሰናይ ገ/መድህን ኤርትራ በዓለም የፕሬስ ነፃነት የሌላት ብቸኛዋ አገር እንደሆነችም ይናገራል፡

እንደ ሰናይ ገለጻ የሻዕቢያ መንግስት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ  የሃሳብ  ነፃነትን ማሰብ   ከህልም የዘለለ አይሆንም፡፡

ቀደም ሲል የፖለቲካ ጥያቄ ያነሱ ዜጎች ለውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆነዋል በሚል   ለስቃይ፣ ለእስርና ለግዲያ  መዳረጋቸውን  ጠቁሟል፡፡

 “በኤርትራ ሚዲያ የህዝብ ጉዳይ የሚስተናገድበት በር ዝግ ነው የደቡብ ህዝብ ከዲቦራ እስከ ዓዲዃላ ያለውን  ለም የጤፍ መሬቱ በሻዕቢያ ወታደሮች በመነጠቁና ንብረቱ በመዘረፉ ፕሬዚዳንቱ ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት ችግሩን ቢገልጽም ሚዲያው በተዛባ መልክ ተጠቅሞበታል፡፡”

በአገሪቱ ማህበራዊ ቀውስ ተባብሶ እያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ጉርሱን በራሽን መልክ በሚጠብቅበት በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ሚዲያ የህልም ኤርትራን  ይስላል ብሏል፡፡ 

የኢሳያስ መንግስት ድህነትን በመቅረፍ ህዝቡን ከመታደግ ይልቅ በጎረቤት አገራት  የማይስፈልግ ጦርነት በማወጅና  የሌሎች አገራትን ተቃዋሚዎች በማደረጀት    ተጠምዷል ብሏል፡፡

የኤርትራ ሚዲያም ይህንኑ ጦረኛ ፖሊሲ ለማስተግበር  በቀጠናው ውጥረት ያነግሳል ያለውን የተዛባ ዘገባ ማቅረቡን እንደቀጠለበት  ጋዜጠኛ ሰናይ ገብረ መድህን ይናገራል፡፡