በአገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጠም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 14 2004 /ዋኢማ/ – በአገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጠም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ገለፀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት መንግስት ያለውን የሕዝብ እድገትና ፍላጎት ትንበያ እንዲሁም የሚጠበቀውን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት በማድረግ ዘርፉን እያለማ ነው፡፡

እስካሁን የኤሌትሪክ ሽፋንን የማዳረስ ስራ በአብዛኛው በተያዘለት እቅድ መሰረት እየተከናወነ ሲሆን ከአምስት አመት በኋላም ይህንኑ ሽፋን 75 በመቶ ለማድረስ የሚስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል፡፡

ይህንኑ እቅድ ለማሳካት ከሚያስችሉ ስራዎች መካከል እንደ ጊቤ ሶስት ያሉ ፕሮጀክቶችም የሚጠቀሱ ሲሆን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና የአገሪቱን ፍላጎት እንዲያሳኩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዚሁ እቅድ አካል የሆነው የገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎችም በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እየተካሔዱ ሲሆን ከአምስት አመት በኋላ የአገሪቱን የኃይል አቅም ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ የተያዘውን እቅድ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የነዚሁ ፕሮጀክቶች መፋጠን የአገሪቱን ፍላጎት ከማሳካት ያለፈ ተግባር ያላቸው ሲሆን በኢትዮ – ኬንያ የኃይል አቅርቦት ስምምነት ብቻ በትንሹ በአመት 250 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮጀክቶቹ የአገሪቱን የስምምነት አቅምና ለዘርፉ የሚያስፈልጋትን ወጪ በመሸፈን ረገድ ሰፊ እገዛ የሚያበረክቱ እንደሆነ አቶ ምሕረት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም በርካታ የሕዝብ ሐብት ፈሶባቸው የሚገነቡ የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና ለታለመላቸው ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ እየተሰራ እንደሆነ መግለፃቸውን  ኢዜአ ዘግቧል።