አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሶስት አገራት ባለስልጣናትን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 17 2004 /ዋኢማ/– ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሶስት አገራት ባለስልጣናትን ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
አቶ ኃይለማርያም ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው የሉክሰምበርግ ምክትል ጠቅይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የጃፓንና የኒውዚላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር የምታደርገውን ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

የሉክሰምበርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን ኤሴበርን እንዳሉት ሉክሰምበርግ ከኢትዮጵ ጋር በተለያዮ መስኮች ያሏትን ግንኙነት አጠናክራ በምትቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሉክሰምበርግ የኢትዮጵያን የአበባ ምርት ለመግዛት የምትፈልግ መሆኑን አመልክተው ከዚሁ በተጨማሪም በተለያዩ የኢንቨስትመንት የልማት ዘርፎችም አብራ መስራት እንደምትፈልግ ገልፀዋል፡፡

አቶ ኃይለማሪያም በመቀጠልም የጃፓን ፓርላማ ምክትል ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩዩሊ ያማን ያነጋገሩ ሲሆን ጃፓን በኢትዮጵያ ውስጥ የምታካሒደውን የልማት ሰራ አጠናክራ እንድትቀጥል ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

ጃፓን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በመንገድ ስራ እያካሄደች ያለችውን ልማት በማጠናከር ወደ ማሕበራዊ አገልግሎቶች በማሳደግ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ እንድትሳተፍ ጠይቀዋል፡፡

የጃፓን ፓርላማ ምክትል ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩዩሊ ያማን በበኩላቸው ጃፓን በኢትዮጵያ ውስጥ የምታደርጋቸውን ልማቶች ወደ ሌሎችም ዘርፎች እንደምታሳደግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የፀጥታ ሁኔታ ላይ የምታከናውናቸውን ተግባራት ለማገዝ ፍላጎት ያለ መሆኑን አመልክተው በተለይም በሶማሊያና በሱዳን ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መስራት እንደምትፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የኒውዝላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙራሪ ኤፍ ሲ በበኩላቸው ኒውዝላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኒውዝላንድ በተለይም በእርሻና በጂኦተርማል ዘርፎች ያላትን ልምዶች በማከፈልና ቴክኖሎጂውን ወደ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር እንዲቻል በሰው ኃይል ልማት ላይ እንደምትሰራ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያም ኒውዝላንድ በእነዚሁ ዘርፎች ያላትን የተሻሻለ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግ እንደምትፈልግም አቶ ኃይለማርያም አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።