በኢትዮጵያ የህንድ ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ጥር 24 2004 /ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ የህንድ ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ ገለፁ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ የሕንድ ባለሀብቶች ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በሕንድ የቼኒ ግዛት አዲስ በተከፈተው የኢትዮጵያ ቆንሲላ ፅፈት ቤት የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ እንደገለፁት በኢትዮጵያ የህንድ ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ።

አዲስ የተከፈተው የኢትዮጵያ ቆንሲላ ፅፈት ቤት የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ወተት እና የወተት ተዋፅኦዎችን በማቀነባበር ፣በጤና፣ በቱሪዝም እና በኬሚካል ኢንዱስትሪዎች  ዘርፍ እንዲሰማሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አምባሳደር ገነት ተናግረዋል።

በሕንድ ቼኒ ግዛት አዲስ በተከፈተው የኢትዮጵያ ቆንሲላ ፅፈት ቤት የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የሕንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮችና ባለሃብቶች ተገኝተዋል።  ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኙ እንደ ህንድ እና ቻይና ባሉት  ሀገራት ላይ ለመድረስ ሰፊና ዕምቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላትም አምባሳደሯ  በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሰሞኑ በሕንድ የሥራ ጉብኝትና የቱሪዝም ዕድሎችን የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ያሉት አምባሳደር ገነት፤ቼኒ በማኑፋክቸሪንግ እና በአውቶሞቲቪ ኢንዱስትሪ እንደመታወቋ ባለሃብቶቿም በኢትዮጵያ በመስኩ መሳተፍ እንደሚችሉ ገልፀዋል።

ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ከአለም ባንክ እና ከሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት የወጡ ሪፖርቶችን በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከቻይናና ከሕንድ በመቀጠል ዘንድሮ በአለም ላይ የምጣኔ ሃብታቸው በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ አገሮች ቀዳሚ መሆኗንም ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት 10 እና 15 አመታት ኢኮኖሚያቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ በማሸጋገር ዜጎቻቸውን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ደረጃ ለማድረስ ትኩረት ሰጥተው ከሚሰሩ አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አምባሳደር ገነት ጠቁመዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በግብርና ላይ የተመሰረተውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

እንደ አምባሳደር ገነት ገለፃ እስካሁን በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ የሕንድ ባለሀብቶች ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛሉ።በእርሻ ፣በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በመዕድን ማውጣት እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት የሕንድ ባለሃብቶች ኢትዮጵያን ወደተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በሕንድ የሎያል ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው ሰላምና ፀጥታ የሰፈነባት፣ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ያላት እና ሕዝቦቿም በተለይ ለህንድ ዜጎች ጥሩ አቀባበል ያላቸው እንደሆኑ ተናድረዋል።

በቼኒ እና በአዲስ አበባ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የእቃ ትራንስትፖርት አገልግሎት መጀመሩን የጠቆሙት በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር  ገነት ዘውዴ በቅርቡ የቼኒ ከተማ ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደምትፈጥር ያላቸውን ተስፋ መግለፃቸውን የዘገበው ዜ ሕንዱ ጋዜጣ ነው።