አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2004/ዋኢማ/– ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ ቼክ ሲዲ ዲያራን ተቀብለው አነጋገሩ።
አቶ ኃይለማሪያም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አመታት ልማትን ለማምጣት እየተደረገ ስላለው ጥረትም ለሚስተር ዲያራ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
በመሰረተ ልማት መስኮች ረገድ በአገር ውስጥ እየተካሄዱ ስላሉት እንቅስቃሴዎችና በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና የልማት እቅዶች በተመለከተም ለሚስተር ዲያራ ነግረዋቸዋል።
በኢትዮጵያ እየታዬ ያለው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴና ለውጥም ለሌሎች በማደግ ላይ ላሉ አገራት ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ገልጸውላቸዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊና በዝቅትኛ የእድገት ደረጃ ላይ ያሉ አገራት፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት እና በማደግ ላይ ያሉ የአነስተኛ ደሴቶች ልዩ አማካሪና ከፍተኛ ተወካይ ሚስተር ቼክ ሲዲ ዲያራ በበኩላቸው ባለፈው አመት ግንቦት ወር መጨረሻ በተመድ አዘጋጅነት በቱርክ ኢስታምቡል ከተማ በተካሄደው በማደግ ላይ ያሉ አገራትና የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ለጉባኤው ስኬት ላደረገችው አስተዋጽኦና ተሳትፎም ምስጋና አቅርበዋል።
ሚስተር ዲያራ በጉባኤው ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ ስምምነት የተደረሰባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች ተግባራዊነት በተመለከተም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በስፋት መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ሁለቱ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእርዳታ ጥገኝነት የምትላቀቅበት ሁኔታ እንዳለና መንግስትም ጠንካራ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች የድርጅቱ ተቋማትም ለኢትዮጵያ ልማት መፋጠን የሚሰጡት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሃሳብ መለዋወጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።