አዲስ አበባ ህዳር 11/2004/ዋኢማ/ – የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ጄኔራል ሳልቫኪር ማያርዲት አዲስ አበባ ሲገቡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሰላምና በክፍለ አህጉሩ ደህንነት ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም የመከሩ ሲሆን፤ ውይይቱን የተከታተሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለፁት፤ ደቡብ ሱዳን አዲስ ሀገር እንደመሆኗ ያሉባትን የአቅም ክፍተቶች ለመሙላት ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን በእኩል ዓይን እንደማየቷ መጠን ለሀገራቱ ሰላምና ብልፅግና መረጋገጥ የበኩሏን እንደምትወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ገልፀውላቸዋል፡፡
በአካባቢው የጋራ ብልፅግና ዕድገት እንዲኖር ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ለማሳደግ በቅርቡ የሁለቱ ሀገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በጁባ መካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ከስምምነት ላይ መደረሱን የኢሬቴቭ ገልጿል።