በአዲስ አበባ ህዳር 19/2004/ዋኢማ/– የኢጋድ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ አልሸባብን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ድጋፍ እንድትሰጥ ጥሪ አቀረቡ። የተካሄደው 19ኛው የኢጋድ መሪዎችን አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ፣ ያልተቋረጠው ኤርትራ ለሽብርተኞች የምታደርገው ድጋፍ እና የሱዳን ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት አተገባበር ሂደት የምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግስታት ኢጋድ 19ኛው አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ዋንኛ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሊቀመንበርነት በተካሄደው ጉባኤ የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር ራምታኔ ላማምብራና የህብረቱ ሊቀመንበር የሶማሊያ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የጋና ፕሬዝዳንት ጄሪ ሮሊንግስ ወቅታዊውን የሶማሊያ የጸጥታና ፖለቲካ ሁኔታን አስመልክቶ ለመሪዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የመከሩት መሪዎቹ ባወጡት የጋራ መግለጫ የኬንያ መከላከያ ሰራዊትና የሶማሊያ ሽግግር መንግስት አሸባሪውን የአልሸባብ ቡድን ለመደምሰስ በጋራ እያካሄዱት ላለው ዘመቻ ኢጋድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
የሽብር ቡድኑን እስከ መጨረሻው ለምደምሰስ ምቹ አጋጣሚ መፈጠሩን የገለጹት መሪዎቹ ለዚህም የዘመቻው ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ተልዕኮውን በጥምረት ሊያካሂዱ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
የኬንያ መከላከያ ሰራዊት የሶማሊያ ሽግግር መንግስትና የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ አሚሶም በጋራ እያካሄዱት ላለው ዘመቻ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግ መሪዎቹ በጋራ መግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኤርትራ ለፅንፈኛ የሽብር ቡድኖች ይበልጥ ደግሞ ለአልሸባብ እያደረገች ባለው እገዛ መቀጠሏን የ19ኛው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ጉባኤተኞች ያስታወቁ ሲሆን፤ በዚህ ድርጊቷ የክፍለ አህጉሩን ሰላም ከማወክ እንድትቆጠብም አሳስበዋል፡፡
በኤርትራ በእስር ላይ የሚገኙ የጁቡቲ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁም ኢጋድ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ የተካሄደው ይህ ጉባኤ ደቡብ ሱዳንን የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ ሙሉ አባል አድርጎ መቀበሉን የኤሬቴድ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።