የአፍሪካ የግብርና ስታትስቲክስ ኮሚሽን 22ኛው አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2004/ዋኢማ/- የአፍሪካ የግብርና ስታትስቲክስ ኮሚሽን 22ኛው አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በመገኘት ጉባኤውን የከፈቱት የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ወንድይራድ ማንደፍሮ እንዳሉት የግብርና ስታትቲስቲካዊ መረጃዎች ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ላይ ለመሰረቱ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ታዳጊ አገራት እጅጉን ጠቃሚና አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ ወቅታዊ፣ አስተማማኝና ጠቃሚ የግብርና ስታትስቲካዊ መረጃዎችን በማሰባሰብ በግብርናው መስክ ስትራቴጂካዊ ውጤቶችን ለማስመዝገብና በዘርፉም አስተማማኝ ውጤት ለማምጣት ልዩ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ መሆኗን ጠቁመዋል።

መረጃው በግብርናው መስክ እቅድ ለማውጣት፣ ቁጥጥር ለማድረግና የተለያዩ ፖሊሲዎችን ለመንደፍም በስፋት እየተጠቀመችበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ድኤታው እንዳሉት ባለፉት አመታት የግብርና ምርት ስታትስቲካዊ መረጃዎች በጥራትም ሆነ በይዘት እየተሻሻሉ ከመምጣታቸውም ባሻገር ለአጠቃላይ የግብርና እድገት አስተዋዕኦ አድርገዋል።

ከዚህ ቀደም በክልልና በወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤቶች በኩል ይወጡ የነበሩ መረጃዎች ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከሚያወጣቸው መረጃዎች ጋር የማይናበቡ እንደነበሩ ያስታወሱት ሚኒስትሩ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን ለማሻሻል በተደረገው ጥረት ይህን ለማጣጣምና ለማስተካከል ማስቻሉን ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳሚያ ዘካሪያ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የግብርናው መስክ የአገሪቱ ዋነኛ የስራ እድል እና የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምግብ ዋስትና ላይ ተጽእኖ ያላቸውን የግብርና መስኮች የመሳሰሉ ዘርፎችን በበቂና ትክክለኛ መረጃ ተደግፎ መተንተን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በግብርና መስኮች ላይ ወቅታዊና አስተማማኝ መረጃ ለመስጠት ብቃት ያለው የመረጃ አሰበባሰብ ዘዴ እጅጉን ጠቃሚ እንደሆነም አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲም በየጊዜው ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመቀጠም የመረጃ ማሰባሰብ ስርዓቱን ለማሻሻል ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የአፍሪካ ክልላዊ ተጠሪ ማሪያ ሄሌና በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በርካታዎቹ የአፍሪካ አገራት የምግብና የእርሻ ስታትስቲክስ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያስችል በቂ ስርዓት የሌላቸውና መረጃዎችን የመጠቀም አቅም ገና አላዳበሩም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የግብርና ስታስቲክስ ኮሚሽን አህጉራዊ ጉባኤን ስታስተናገድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የአፍሪካ የግብርና ስታትስቲክስ ኮሚሽን የተቋቋመው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1962 ሲሆን፤ ጉባኤው የፊታችን ቅዳሜ ይጠናቀቃል ሲል የኢዜአ አገልግሎት ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።