16ኛ አለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ 2011/አይካሳ/ ጉባኤ ተጀመረ


አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2004/ዋኢማ/
16ኛው አለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ 2011/አይካሳ/ ጉባኤ በርካታ እንግዶች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ በሚሌኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፈተ።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሚሼል ሲዲቤ በአፍሪካ ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ተጨባጭ የሆነ እንቅስቃሴ ሴደረግ እንደነበር ቀደም ሲል  የተሰሩ ስራዎችና ከውጤቶቻቸው ማየት ተችሏል ብለዋል።

ቀደም ባሉት አመታት በአፍሪካ ኤችአይቪ/ኤድስን መከላከልም ሆነ መቆጣጠር እንደማይቻል ይገለፅ እንደነበር ጠቁመው፤ አሁን እየታየ ያለው አበረታች ውጤት ቀደም ሲል ይታሰብ የነበረውን አመለካከት መለወጠቱን   ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ መመጣቱንና የጸረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ተጠቃሚዎችም ቁጥር ባስገራሚ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ የስራው ውጤት ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀደም ባሉት አመታት ኡጋንዳና ሴኔጋል የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን በመቆጣጠር ረገድ ከአፍሪካ አህጉር ይጠቀሱ እንደነበር ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ25 በላይ የሚሆኑ ሀገራት የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ችለዋል መቻላቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍና ህፃናት ከቫይረሱ ነፃ ሆነው እንዲወለዱ በአፍሪካ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እየታየበት መሆኑን ጠቁመው፤ በአህጉሪቱ አስገራሚ ለውጥ መገኘቱንም አመልክተዋል፡፡

ኤችአይቪ/ኤድስ በአፍሪካ የበርካታ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉን ያስታወሱት ሲዲቤ፤ በተከናወኑት በርካታ ስራዎች የቫይረሱን ስርጭት ፍጥነትና በፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት እጦት ምክንያት የሚጠፋውን ህይወት መታደግ ተችሏል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን በመከላከሉና በመቆጣጠር በኩል አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።

ለውጤቱም በመላው ሀገሪቱ የተሰማሩት 34ሺ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በህብረተሰቡ ውስጥ መሰማራታቸውና ውጤታማ ስራ መስራታቸው ለአብነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትና መከላከሉና በመቆጣጠሩ ረገድ የተጀመረው ስራ ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ   እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገልፀዋል።

16ኛ አለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ 2011/አይካሳ/ ጉባኤ  «OWN SCALE UP and SUSTAIN» በሚል መሪ ቃል ለአምስት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

ዋኢማ

አዓ