በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ተጣለ

አዲስ አበባ ህዳር 26/2004/ ዋኢማ/– የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ትናንት በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሉ ተገለፀ።

የተባበሩት መንግስታት የዜና ማዕከልን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደዘገበው፤ ኤርትር የምስራቅ አፍሪካና የሱማሌያ የፀጥታ ሁኔታን ለማናጋት የተደራጁ ፀረ-ሰላም ሀይሎችን በመደገፍ እያደረገች ባለው ፀረ- ሰላም እንቅስቃሴ ምክንያት የፀጥታው ምክር ቤት ትናንት ተጨማሪ ማዕቀብን ጥሏል።

ማዕቀቡ የተጣለው እንደ አልሸባብና ሌሎች በምስረቅ አፍሪካ ሀገራት አካባቢ ሰላም እንዳይኖር ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሰ ፀረ-ሰላም ሀይሎች በምታደርገው ድጋፍ ነው።

ኤርትራ ለአሸባሪው የአልሸባብ ቡድን እያደረገች ያለውን የፖለቲካ፣ የገንዘብ፣ የስልጠና እና የሎጂስቲክ ድጋፍ አጠናክራ በመቀጠሏ ማዕቀቡ እንደተጣለባትም የዜና ማዕከሉ ጠቁሟል።

የፀጥታው ምክር ቤት አባል ከሆኑ 15 ሀገራት መካከል በ13ቱ ተጨማሪ ማዕቀቡ እንዲጣል የይሁንታ ድምፅ የሰጡ ሲሆን፤ ሁለት ሀገራት ማለትም ቻይናና ሩሲያ ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸውን የዜና ማዕከሉ ገልጿል።

እንዲሁም ኤርትራ የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ጥር አዲስ አበባ ሊካሄድ የነበረውን የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ለማደናቀፍ ያደረገችውን ሙከራም አውግዟል።

የሶማሊያንና የኤርትራን ጉዳይ ለማጣራት የተቋቋመው ቡድን እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ አጣሪ ቡድን  የኤርትራ መንግስት የተለያዩ ስብሰባዎች በሚካሄድበት ወቅት፣ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎችና ሰላማዊ ወገኖችን ለማወክና የመንግስት ተቋማትን ኢላማ ያደረጉ የተለያዩ የቦንብ ጥቃቶችን ለማድረስ አቅዶ እንደነበር የአጣሪ ቡድኑ ምርመራ ማረጋገጡንም ገልጿል።

እ.ኤ.አ ባለፈው ታህሳስ 2009 የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ በሶማሊያ የሚገኘውን የሽግግር መንግስት ለመጣል ለሚታገሉ የፀረ-ሰላም ሀይሎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረጓ ማእቀብ መጣሉ የሚታወስ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።