ሕገ-መንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱን ይበልጥ ማስተዋወቅና ተቋማዊ እምነት መፍጠር ትኩረት የሚሰጠው መሆኑ ተገለፀ

መቀሌ፤ ህዳር 28/2004/ዋኢማ/ – ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሲከበር ሕገ-መንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱን ይበልጥ ማስተዋወቅና ተቋማዊ እምነት መፍጠር ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አስታወቀ።

አፈ-ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ህዳር 29 የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት አዳራሽ የተዘጋጀውን የሁለት ቀናት ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም በከፈቱበት ዕለት በህገ-መንግስቱ ላይ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አፈ-ጉባዔው እንደገለፁት የዘንድሮውን በዓል ከሌሎቹ የሚለየው ህገ-መንግስቱን በስፋት በማስተዋወቅ በሚያስችሉ የተለያዩ ዚምፖዚየሞች ታጅቦ በደመቀና በመላው ህዝብ ተሳትፎ የሚከበር በዓል መሆኑ ነው ብለዋል።

“ህገ-መንግስታችን ላይ የጠራ ግንዛቤ መያዝ፣ የህገ-መንግስቱን ተራማጅነትና ዘመናዊነት በይዘቱ ያለውን ጥብቅ ዴሞክራሲያዊ ገፅታ እንዲሁም ለሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ሰፊ መሰረት የጣለ መሆኑን ለማሳየት በህገ መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የሚሰነዘሩ የተዛቡ አስተሳሰቦችን በትክክለኛ አመለካከት መተካት ያስፈልጋል” በማለት አፈ ጉባዔው ገልፀዋል።

ህገ-መንግስቱን በማስተማር ዙሪያ እስካሁን የተሰራው ስራ በቂ አለመሆኑን ያወሱት አፈ-ጉባዔው የህግ የበላይነት፣ በምክያታዊነት፣ በመቻቻልና ልዩነት የሚፈታ ትውልድ የመገንባትና መብትና ግዴታውን  የሚያውቅ ህብረተሰብ ከመፍጠር አንፃር ቀሪ ስራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አስታኮ በመላው ሀገሪቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ሲምፖዚየም በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አማካኝነት የተካሄደ ሲሆን፤ ከ25 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችም ቀርበዋል።

ሲምፖዚየሞቹም አስተማሪና ገንቢ ውጤት የታየበት መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔው አቶ ካሳ ተክለብርሃን ተናግረዋል።

በከፍተኛ መስዋዕትነት የዜጎችን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች የተረጋገጡባት አዲሱቷ ኢትዮጵያ እውን መሆኗን ተናግረው፤ ለዚህም ህገ-መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱ መሰረት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ዛሬ በተጀመረው ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም 10 የሚሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የዲያስፖራ ጉዳዮች አማካሪ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴን ጨምሮ በሌሎች ምሁራንም ጥናታዊ ፅሁፎቹ እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የተዘጋጀው ሲምፖዚየሙ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በማድመቅ በኩል ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

ሲምፖዚየሙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣን፣ የክልል መስተዳድሮችና የመንግስት ባለስልጣናትና ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።