በኤርትራ መንግስት ላይ የተጣለው ማእቀብ የአገሪቱ መንግስት የአካባቢውን አገራት ከማተራመስ ተግባሩ እንዲታቀብ የሚያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2004/ዋኢማ/-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ መንግስት ላይ የጣለው ማዕቀብ የአገሪቱ መንግስት የአካባቢው አገራትን ከማተራመስ ተግባሩ እንዲታቀብ የሚያደርግ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ እስካሁን ምንም አይነት የኢትዮጵያ ሰራዊት ወደ ሶማሊያ አለመግባቱንም ይፋ አደረገ፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  እንዳመለከቱት፤ የኤርትራ መንግስት የሚያደርገውን አካባቢውን የማተራመስ ተግባር ባያቆም ማእቀቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሔዳል፡፡

በማእቀቡ የኤርትራ መንግስት በአካባቢው አገራት ሽብርና ግርግር ለመፍጠርና የራሱን ሕዝብ የስቃይ ሰለባ ለማድረግ የሚጠቀምበትን ከማዕድን ሽያጭ ገቢና የዳያስፖራ ታክስ ገቢ መታገዱ ለኤርትራ ሕዝብና ለአካባቢው አገራት ሰላም እንደሚያመጣ አስረድተዋል፡፡

የኤርትራ መንግስት በውጭ አገር የሚገኙ ኤርትራውያን የሚለግሱትን የዳያስፖራ ታክስ ለሶማሊያ አሸባሪ ቡድኖችና በአካባቢው ባሉ ሌሎች አገራት ለሚገኙ አክራሪ ኃይሎች መሳሪያና ሌሎች ድጋፎች መግዣ እያደረገው መሆኑንም እንደተደረሰበት ገልፀዋል፡፡

በኤርትራ የማእድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ አገራት ከዚሁ የሚገኘውን ገንዘብ ለኤርትራ መንግስት ሲሰጡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ያለባቸው ሲሆን ይህንኑ አሰራር በተመለከተና ወደ አገሪቱ የሚወጣና የሚገባ ማንኛውም ገንዘብ ላይ አገራት እንዲፈትሹና ለታዛቢ ቡድኑ ሪፖርት እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡

ሁሉም የኢጋድ አባል አገሮች ውሳኔው በአንድ ድምጽ ያሳለፉ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አባል አገራቱ የኤርትራ ሕዝብ በተጣለው ማእቀብ ምክንያት እንዳይጎዳ ትልቅ ጥንቃቄ አድርገዋል ብለዋል፡፡

ለዚህ ማሳያ ደግሞ ውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ በማእቀቡ ውስጥ እንዲካተት አለመደረጉን ገልፀዋል፡፡

ማእቀቡ የተጣለው ኤርትራ በአካባቢው በተለይም በኢጋድ አባል አገራት ላይ እየተጫወተች ያለችውን አፍራሽ ሚና በተመለከተ እንዲከታተልና ለምክር ቤቱ በየስድስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ የተሰየመው የመንግስታቱ ድርጅት አጣሪ ቡድን ባቀረባቸው ማስረጃዎች በመደገፉቸው ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የኢጋድ አባል አገራት በኤርትራ ሕዝብ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዲደርስባቸው እንደማይፈልጉም አመልክተው የኤርትራ እድገትና ብልጽግና ለኢትዮጵያም መሆኑን እናምናለን ብለዋል፡፡

በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ሁሉም አገራት ለተባበሩት መንግስታት ሪፖርት የሚያደርግ ሲሆን ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ ታዛቢ ቡድኑ ኤርትራ ማእቀቡን ካልተገበረች ለምክር ቤቱ በማሳወቅ ተጨማሪ ማእቀብ እንደሚተላልፋባት አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያም ሆነ የኢጋድ አባል አገራት በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞንን በየአገሮቻቸው እያስተናገዱ መሆኑንና የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በየትኛውም የአካባቢው አገራት ሕዝብ ላይ ችግሮች እንዲፈጠሩበት አይፈልጉም ብለዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ብቻ አንድ ሺህ የሚሆኑ ኤርትራውያን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እንዲማሩ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡

እስካሁን ምንም አይነት የኢትዮጵያ ሰራዊት ወደ ሶማሊያ አለመግባቱን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው ነገር ግን ኢትዮጵያ በኢጋድ ጥያቄ መሰረት የምትጠየቀውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ውስጥ ያለው የሽግግር መንግስቱና አልሸባብን የሚታገሉ የተለያዩ የሰላም ኃይሎች በአንድነት በመሆን አልሸባብን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳከሙ መምጣቸውን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ባለፈው ሳምንት በኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የሶማሊያን የሽግግር መንግስትና ሌሎች የሰላም ኃይሎችን እንድትደግፍ መጠየቋን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኢጋድና የአፍሪካ ሕብረት ታማኝ አባል አገር በመሆኗ ድርጅቶቹ የሚሰጡዋትን ውሳኔና ተልአኮ በማሳካት በኩል የምትጠየቀውንና ድጋፍ እንደምታደርግም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የሽግግር መንግስት ምን አይነት ድጋፍ መስጠት እንዳለባት የምትመረምር ሲሆን ጥያቄው ሰራዊት እንድትልክ ከሆነም እንደምትቀበለው ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ሰራዊቷን የምትልክ ቢሆንም ለረዥም ጊዜ የመቆየት አላማ የሌላት ሲሆን ሌሎች ኢጋድ የሚጠይቀውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ በርካታ ችግሮት ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱን አመልክተው፤ የሽግግር መንግስቱም ሆነ ሌሎች የሰላም ኃይሎች በአግባቡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን ሚኒስቴር ዴኤታው መጠቆማቸውን የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።