የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አባል ሀገራት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች ጉባኤ ተጀመረ

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2004/ዋኢማ/ – በአዲስ አበባ የተጀመረው የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አባል ሀገራት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች ጉባኤም የተጠንቀቅ ኃይሉን አመታዊ የስራ ክንውን እና እ.ኤ.አ በ2015 በሙሉ ኃይሉ ግዳጅ ለመፈጸም የሚችል ሰራዊት የመገንባቱን ሂደት ይገመግማል፡፡

በክፍለ አህጉሩ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ በይበልጥ ደግሞ በሶማሊያ ሁኔታ ላይም በሰፊው ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ሜጄር ጀነራል ሲሪል ንዳይሩኪዬ እንዳሉት በክፍለ አህጉሩ ሰላም እና መረጋጋት ለማስጠበቅ የሚችል ኃይል ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ አባል ሀገራት ጠንካራ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡

የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሊቀመንበር ጄኔራል ሳሞራ የኑስ እንዳሉት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር የክፍለ አህጉሩ የወቅቱ አደጋዎች የሆኑት ሽብርተኝነት እና የባህር ላይ ወንብድና ሊያስወግዱ ይገባል፡፡

ለዚህም 2 አስርት ዓመታትን ላስቆጠረው የሶማሊያ ቀውስ መፍትሄ በማፈላለጉ ሂደት ሁሉም አባል ሀገራት ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡

የጉባኤው የክቡር እንግዳ የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስትር ሲራጀ ፈርጌሳ የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል የወቅቱ የክፍለ አህጉሩ ሰላም እና ደህንነት ቁልፍ ችግር ለሆነው የሶማሊያ አለመረጋጋት መፍትሄ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ሃይል 10 ሀገራትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2015 በክፍለ አህጉሩ ሰላም አና ፀጥታን ለማስከበር እንዲሁም ግጭትን ለማስወገድ የሚችል ኃይልን አቋቁሞ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት እየሰራ እንደሚገኝ የኢሬቴድ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።