በምስራቅ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተቀላጥፎ እንዲቀጥል የኢጋድ መሪዎች አስገነዘቡ

አዲስ አበባ፤ጥር 19 2004 /ዋኢማ/– 20ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን/ኢጋድ/ ልዩ የመሪዎች ጉባዔ በክፍለ አህጉሩ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተቀላጥፎ እንዲቀጥል አስገነዘበ፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ትናንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በኢጋድ አባል አገራት ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል መሪዎቹ አስገንዝበዋል፡፡

ነፃ የንግድ ቀጣናው በታለመለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ሥራውን እንዲጀምር መሪዎቹ ማሳሰባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አመልክተዋል፡፡

ውህደቱን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማሳካትም የአካባቢውን አገራት በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ መሪዎቹ ማስገንበዛቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢጋድ መሪዎች የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ስትራቴጂው አሁንም እንደቀጠለ ምክር ቤቱ ተገንዝቦ በዚህ አሸባሪ መንግሥት ላይ የጣለውን ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት፣ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ኃይልና የኬንያ መከላከያ ኃይል በደቡብና በማዕከላዊ ሶማሊያ በቅንጅት ያስገኙትን ድል መሪዎቹ አወድሰዋል፡፡

በሽግግሩ መንግሥት ጥሪ መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ለሰጠው ፈጣን ምላሸ የኢጋድ መሪዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን መንግሥታት በተናጠል የሚያካሂዷቸውን ተግባራት ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል በደረሱት አጠቃላይ የሠላም ስምምነትና ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖረውን አግባብ የሚጻረር በመሆኑ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የኢጋድ መሪዎች ጠይቀዋል፡፡

ሁለቱ አገራት እየሻከረ የመጣውን ግንኙነታቸውን በማሻሻል በቀሪ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ውይይት ለማድረግ በጉባዔው መስማማታቸው የኢጋድ መሪዎችን አስድስቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአቢዬ ግዛት ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሠላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት እያደረገች ያለውን ጥረት መሪዎቹ አድንቀዋል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው በዚሁ ጉባዔ የኬንያው ፕሬዚዳንት ሙዋይ ኪባኪ፣ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኡመር ሐሰን አልበሽር፣ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦመር ጌሌህ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትና የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ሼህ ሸሪፍ ሼህ አህመድ መገኘታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡