አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንጻ በደማቅ ስነስርዓት ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2004 (ዋኢማ) -አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንጻ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የቻይና ህዝባዊ አማካሪ ጉባኤ ሊቀመንበር ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ባለስልጣናት በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት ተመረቀ፡፡

በስነስዓቱ ላይ የቻይና ህዝባዊ አማካሪ ጉባኤ ሊቀመንበር ዢ ኩዊንግ ሊንግ ለምልክትነት የተቀመጠውን ቁልፍ ለወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አስረክበዋል፡፡

የህንጻው ሙሉ የግንባታ ወጪ እና የቢሮ እቃዎች በቻይና መንግስት የተኘፈነ ሲሆን ኢትዮጵያ ለህንጻው መገንቢያ የሚሆነውን መሬት በነጻ ከመስጠት ጀምሮ የግንባታ እቃዎች በነጻ እንዲገቡ በመፍቀድ ጉልህ ሚናን ተጫውታለች፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እንዳሉት የህንጻው መገንባት በአፍሪካ አህጉር ላይ ብሩህ ተስፋን የሚፈነጥቅና የአፍሪካን ህዳሴ ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዣን ፒንግ በበኩላቸው አዲሱ ህንጻ ህብረቱ የነበረበትን ከፍተኛ የሆነ የቢሮዎችና የመሰብሰቢያ አዳራሾች ችግር ከመቅረፍ ባለፈ አፍሪካና ቻይና ያላቸውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል ብለዋል፡፡

የቻይና ህዝባዊ አማካሪ ጉባኤ ሊቀመንበር ዢ ኩዊንግ ሊንግ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት አዲሱ ህንጻ ሀገራቸው ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸው ወደፊትም ሀገራቸው ከአህጉሩ ጋር የላቀ ግንኙነት ለመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው የአፍሪካ ህብረት ህንጻ የመሬትና የቀረጥ ነጻ ተመንን ሳይጨምር 200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጥቶበታል፡፡

ህንጻው እ.አ.አ በ2009 የተጀመረ ሲሆን በ112,000 ስኩዌር ሜትር ላይ አርፏል፡፡ ህንጻው 2,500 ሰዎችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም ያለው የመሰብሰቢያ አዳራሽና መካከለኛ ስብሰባዎችን የማስተናገዱ አዳራሾችንም ይዟል፡፡

በተጨማሪም 2,500 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው አምፊ ቲያትር እና የሂሊኮፕተር ማረፊያ ቦታ መያዙንም ኢሬቴድ ዘግቧል፡፡