አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 17 2004 /ዋኢማ /- የኢትዮ-ሱዳን ሁለተኛው የጋራ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ በካርቱም መካሔዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ትናንት እንዳስታወቀው የኢትዮ-ሱዳን ሁለተኛው የጋራ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ከታኅሣሥ 12 እስከ 15 ቀን 2004 ዓ.ም በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአቶ ኃይለማርም ደሳለኝ የተመራ ሲሆን ከእርሳቸው ጋር የፖለቲካ ኮሚቴ አባላት ሚኒስትሮች ተገኝተዋል፡፡
የሱዳን የልኡካን ቡድን ደግሞ በሚስተር ዓሊ አሕመድ ካልፊ ተመርቷል። በተመሳሳይ መንገድ የተለያዩ ሚኒስትሮች በልኡካን ቡድኑ መካተታቸውን አስታውቋል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ሁለት የመግባቢያ ሰነዶች መፈረማቸውን የገለፀው የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ሌሎች ሁለት የስምምነት ረቂቆች በሚቀጥሉት 60 ቀናት እንዲፈረሙ ሲወሰን አምስት የድርጊት መርሃ ግብሮች በማውጣት ማጽደቁንም አብራርቷል፡፡
ሁሉቱም ወገኖች በተነሱት የጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የተወያዩ ሲሆን የእነዚህ ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ታምኖበታል፡፡
የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተለይም የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር በገዳሪፍ፣ ደማዚን፣ ጎንደርና ባሕር ዳር ላይ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት መግባባት ላይ መደረሱን አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በፀጥታና ደህንነት አጠባበቅ ሁለቱም አገራት ያላቸው ግንኙነት ጥሩ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መወሰናቸውንም ሚኒስቴሩ አስታዉቋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚሁ ወቅት የሱዳኑን ፕሬዚዳንት አልበሽርን በማግኘት በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዩች ላይ ጠቃሚ የሆነ ውይይት አካሒደዋል፡፡
ቀጣዩ ስብሰባ በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት አዲስ አበባ ላይ እንዲካሔድ መወሰኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ የዘገበዉ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነዉ።