የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የ11 አመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተላለፈ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 17 2004 /ዋኢማ / -ለአሸባሪው የኦብነግ ታጣቂ ድጋፍ በመስጠትና የሉአላዊ አገርን ህግ ጥሶ በመግባት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ሁለት የስዊዲን ጋዜጠኞች ላይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት በአስራ አንድ አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ዉሳኔ አስተላለፈ።

ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬና የፎቶ ጋዜጠኛ ጁሀን ፐርሰን ከለንደን የአሸባሪው የኦብነግ ሀላፊ ጋር በመገናኘት ከዚያም ኬኒያ ደርሰው ወደ ሱማሌ ክልል በመግባት ለቡድኑ ድጋፍ መስጠታቸውንና በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው በመረጋገጡ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ባለፈው ሳምንት ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃዎች ጋዜጠኞቹ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸውና ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱ በመሆናቸው የቅጣት ውሳኔ እንዲቀልላቸው የጠየቁትን ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ እያንዳንዳቸው በአስራ አንድ አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል አቃቤ ህግ በተከሳሾች እጅ የተገኙ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት በጠየቁት መሰረትም ተከሳሾች ተቃውሞ የለንም በማለታቸው ንብረቱ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ላይ ተከሳሾች ይግባኝ የማለት መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡