አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 18 2004 /ዋኢማ/ – የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን ማዕከል በማድረግ መንግሥት የነደፈውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መደገፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ያደመጠ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በኩል ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮችን በመለየት ለተጀመረው ፈጣን ልማት አስፈላጊ የሆኑ የመሠረተ ልማት፣ የምህንድስናና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማስገኘት ያካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ሥራ የሚያበረታታ ነው፡፡
አገሪቷ እያካሄደች ባለችው የልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥረትና በአስተማማኝ ሰላሟ ላይ ጉልህአስተዋጽኦ ማበርከት ከሚችሉ አገሮች ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነት በመፍጠር ረገድ የሚደነቅ ተግባር ማከናወኑንም ምክር ቤቱ አመልክቷል፡፡
በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በአገሪቷ ያለውን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በማሰተዋወቅ የውጭ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ አስችሏል፡፡
በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮችና አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባትን በማጎልበት ለአገር ልማት የበኩላቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያከናወናቸው ተግባራት ጠቃሚ መሆናቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
የኤርትራ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ የሚከተለውን እኩይ ድርጊት የዓለም ማህበረሰብ እንዲገነዘበው በማድረግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣልበት ያካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ስኬታማ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ያም ሆኖ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ በአገራዊ ልማት ተሳትፏቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ሚኒስቴሩ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት ምክር ቤቱ አስገንዝቧል፡፡
በተመሳሳይም ሚኒስቴሩ የልማታዊ ዲፕሎማሲ ሠራዊት ለመገንባት እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራበት ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ቀጣይና የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ አንጻር የዲያስፖራ ረቂቅ ፖሊሲ ተቀርጾ ከባለድርሻ አካላትና ከዲያስፖራው ጋር ሰፊ ውይይትና ምክክርየተደረገ ሲሆን፣ በውይይቱ የተገኙትን ገንቢ አስተያየቶችን በማካተት በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡
የልማታዊ ዲፕሎማሲ ሠራዊት ግንባታን በተቀላጠፈ ሁኔታ እውን ለማድረግ የሚያስችል የንቅናቄ መፍጠሪያ ሰነድ መዘጋጀቱንም ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡