አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19 2004 /ዋኢማ/ – ጋና እና ኢትዮጵያ የቆየውን ግንኙነታቸውን በንግድ ልውውጥ ዘርፍ በማጠናከር ለሕዝቦቻቸው ጠቃሚ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚችሉ አምባሳደር ጊፍቲ አባሲያ አስታወቁ።
ሁለቱ አገሮች ሕዝቦቻቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉ በርካታ የሥራ ዕደሎች እንዳላቸዉም አምባሳደሯ ተናግረዋል።
አምባሳደር ጊፍቲ አባሲያ ዴይሊ ግራፊክ ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ የጋና መንግሥት ኦፊሴላዊ ፖርታል አሥፍሮ እንዳስነበበው ኢትዮጵያ በጋና የማይገኙ በርካታ አበባዎችን ከማምረት ጀምሮ የቆዳ ውጤቶች፣ ትኩስ ፍራፍሬና ሌሎችም የግብርና ውጤቶችን ጥሩ መሠረት ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት ማቅረብ ትችላለች።
ጋና ለምታመርታቸው የጎማ ምርቶች፣ የወጥቤት ዕቃዎች፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችና ሌሎችም ምርቶች 85 ሚሊየን ያህል ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ ናት ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጋና ከመብረሩ ውጪ በሁለቱ አገሮች መካከል የንግድ ልውውጥ አለመኖሩን የጠቀሱት አምባሳደሯ የቆየውን ግንኙነታቸውንና ወዳጅነታቸውን በማጠናከር በንግድ ልውውጥ ለሕዝቦቻቸው ጠቃሚ የሥራ ዕድሎች መፍጠር እንደሚችሉ አመልከተዋል።
በጋና የኢትዮጵያ ኤምባሲ የጋና የንግድ ሚኒስቴር እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አባላት ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር እንዲገናኙና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ንግግር መጀመሩን መግለፃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።