በሁለቱ የስዊዲን ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈው ውሳኔ የአገራቱን ግንኙነት እንደማያሻክረው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20 2004 /ዋኢማ/ – የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የወንጀል ችሎት በሁለቱ የስዊዲን ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈው ውሳኔ  የኢትዮ ስዊዲንን ግንኙነት እንደማያሻክረው የኢፊዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

የአገራቱ ግንኙነት ከፍርድ ሂደቱ ጋር ሊያያዝ እንደማይገባው የገለጹት አቶ ሀይለማርያም ከዚህ በፊት የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተወሰነ ደረጃ ሻክሮ መቆየቱን አስታውሰው የአገራቱ ግንኙነት ከፍርድ ሂደቱ ባሻገር ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጋዜጠኞቹ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡት ውጊያ ላይ ካለውና አልሸባብን ከሚረዳው ከኦብነግ ጋር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪም መሳሪያ ይዘው መግባታቸው በቪዲዮ ማስረጃ ተረጋግጦ በፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው እንደተፈረደባቸው ገልጸዋል። አያይዘውም ፍርድ ቤቱ የፍትህ ስርአቱን ከማጎልበት አንጻር ማድረግ የሚችለውን መስራቱን ተናግረዋል።

ሂዩማን ራይትስዎችና አንዳንድ ድንበር ዘለል የጋዜጠኞች ማህበራት በፍርድ ውሳኔው ላይ የሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት ይሉት የነበረውና አዲስ ነገር እንደሌለው ጠቅሰው የስዊዲን መንግስትም የፍርድ ሂደቱን ከመከታተል ውጭ ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው ጥያቄ እንደሌለ አስታውቀዋል።

አቶ ሀይለማርያም ከስዊዲን መንግስት ጥያቄ ከቀረበ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንሰጣለን ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ህብረት ጋዜጠኞችን ለማስፈታት ጥረት እንደሚያደርግ መግለጹን ተከትሎም ህብረቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ህግ የመጻረር መብት እነደሌለው አስታውቀዋል።

አቶ ሀይለማርያም የአውሮፓ ህብረት በተለመደው የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ዲያሎግ መካኒዝም አንቀጽ ስምንት ከመነጋገር ውጭ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል።

ጋዜጠኞቹ የተያዙት በውጊያ ላይ ቆስለውና አንደኛው ከዚህ በፊት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ ሲገባ ተይዞ ምህረት ተደርጎለት መውጣቱንም አስታውሰዋል።

በጋዜጠኞቹ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ የአውሮፓ ህብረትንና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የልማት አጋርነት አደጋ ላይ ይጥለዋል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው አቶ ሀይለማርያም መናገራቸዉን የዘገበዉ ኤፍ ቢ ሲ  ነዉ።