አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/ – የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት የበረራ አስተናጋጅ ወይዘሮ አበራሽ ሀይላይ የቀድሞ የትዳር አጋር ፍስሃ ታደሰ ላይ የ14 አመት ፅኑ እስራት በየነ።
ችሎቱ በትናንት ውሎው ብይን የሰጠዉ በከባድ የግድያ ሙከራ እና ያልተፈቀደ መሳሪያ መያዝ በሚል በተመሰረተበት ክስ ነዉ።
ችሎቱ ለትናንት ውሎው የአቃቢ ህግንና የተከሳሽ ጠበቃን ቅጣቱ ይክበድልንና ይቅለልልን የሚለውን አስተያየት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል።
አቃቢ ህግ ከሰባት የማያንሱ ቅጣቱ ይክበድልን በሚል ያቀረባቸው ዝርዝር ሀሳቦች ተከሳሽ ወንጀሉን ዘግናኝ በሆነ መልኩ መፈጸሙን የሚያመላክቱ ናቸው።
በሌላ መልኩ የተከሳሽ ጠበቃ ተከሳሽ ወንጀሉን በፈጸመበት ሰአት በራሱ ተነሳሽነት ለህግ ማሳወቁ፣ በደርጊቱ መጸጸቱን፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደሙ ውስጥ እንዳለበትና ከዚህ በፊት ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ እንደሌለበት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ችሎቱ የሁለቱን ወገን አስተያየት መርምሮ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቅጣት አወሳሰንን በተመለከተ ያወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ አቃቢ ህግ ካቀረበው የይክበድልኝ ጥያቄ በመመሪያው መሰረት አንድ እርከን ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል።
እንዲሁም የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረባቸውን የቅጣት ይቅለልልኝ ጥያቄ ስምንት እርከን ዝቅ አድርጎ ተመልክቶታል።
በዚህም መሰረት ምንም እንኳን ተከሳሽ የፈጸመው ድርጊት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 27 እና 539 መሰረት እድሜ ልክ ወይም በሞት የሚያስቀጣ ቢሆንም ዝቅ ካለው እርከን በመነሳት ድርጊቱ ከ12 እስከ 14 አመት ከአምስት ወር በሚለው ቅጣት ላይ ይወድቃል።
ይህን ግምት ውስጥ በማስገባትም ችሎቱ ተከሳሽ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ 14 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
ወንጀሉ ሲፈጸም በኤግዚቢትነት የተያዘው አንድ ስታር ሽጉጥም ለመንግስት ውርስ እንዲሆን ችሎቱ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል ።